post

የሀገር ውስጥ የባንክ ዘርፍ ለውጪ ባንኮች መከፈት እድልና ተግዳሮቱ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ከመፈቀዱ ጋር ተያይዞ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ባለሙያዎች ፖሊሲው ከመተግበሩ በፊት ዳግም በእድሎቹና ተግዳሮት ዙሪያ መፈተሽ ያለባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ፖሊሲውን ለመተግበር የወጡ ረቂቅ መመርያዎችን ተከትሎ በጉዳዩ ላይ በተዘጋጁ የውይይት መድረኮች ላይ የውጭ ባንኮች አገባብ ላይ መንግሥት ጥንቃቄ ያድርግ የሚባለው ግፊት እየጨመረ መምጣቱንም ለመረዳት ተችሏል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበር ምክር ቤት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ እንደተናገሩት ባለፉት በርካታ አስርት አመታት ሀገራችን በሯን ለውጭ የፋይናንስ ተቋማት ዝግ ማድረጓን ገልጸው ንግድ ምክር ቤታቸው የውጪ ባንኮች በሀገራችን የባንክ ዘርፍ ቢሳተፉ ከሚኖር ተግዳሮት ጎን ለጎን የሚገኙ እድሎችም እንዳሉ እንረዳለን ብለዋል፡፡
በተለይ ‹‹የግል ባንኮች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?፣ የሚኖረው የውድድር አውድ እስከምን ድረስ ነው? የሚለው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግሥት ይህንን ዕርምጃ ዕውን ማድረጉ ምን ጥቅም ያስገኛል? ምንስ ያሳጣል? የሚለው የአባሎቻችንም ሆነ የንግድ ምክርቤታችን ጥያቄ መሆኑን አውስተዋል፡፡
በእርግጥ የውጭ ባንኮች በሀገራችን መግባታቸው ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጥርጥር ባይኖርም አገባባቸው ግን የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ይህም አጠቃላይ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ከማሳደግና ለአገር ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር ታይቶ የሚወሰድ ዕርምጃ ይሆናል ብለንም እንገምታለን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በፓናሉ ተናጋሪ ከነበሩት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች መካከል ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው እንደገለጹት ከውጭ ባንኮች መግባት ጋር በተያያዘ ሦስት ዋና ዋና ተግዳሮቶች ይገጥማሉ፡፡
ሊገጥሙ የሚችሉት ችግሮች የማክሮ ፋይናንስ መዛባት፣ በባንኮቹ ውስጥ ያለው ችግርና ከብሔራዊ ባንክ አቅም ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ጠቁመው፣ እንዲህ ያሉ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ የውጭ ባንኮችን ማስገባት ከባድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የውጭ ባንኮች መግባት ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም የተለያዩ ጥናቶች የሚያመለክቱ ግን የሚባለውን ያህል ጥቅም የሚያመጣ አለመሆኑንና በተለይ የማክሮ ኢኮኖሚው ባልተረጋጋበት ሁኔታ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የሚፈቅደውን ፖሊሲ መተግበር ጉዳት ያመጣል የሚል እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡
ከማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ጋር የተያያዙት የዋጋ ንረት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ጦርነት የኢኮኖሚ ውጥኑን ለማስፈጸም ፈታኝ እንደሚሆኑም ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል፡፡
በዚህ መድረክ ላይ ሌላው ማብራሪያ የሰጡት የአሐዱ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ እሸቱ ፋንታዬ፣ አሁን ባለው ሁኔታ የውጭ ባንኮች ይግቡ ማለት ብዙ ችግሮች ያስከትላል የሚል እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡
በተለይ ለዓመታት የገንዘብ ፖሊሲው ችግር ያለበት ሆኖ ከመቆየቱ አንፃር የውጭ ባንኮችን ማስገባት መፍትሔ እንደማይሆንም ጠቁመዋል፡፡
የውጭ ባንኮች መግባት የለባቸውም የሚል እምነት እንደሌላቸው ያመለከቱት አቶ እሸቱ ነገር ግን አሁን እንዲገቡ የሚፈለግበት መንገድ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል ብለዋል፡፡
ይህ ፖሊሲ ወደ 500 ሺሕ የተጠጉ የባንክ የአክሲዮን ባለቤቶችን መብት ሊያስጠብቅ መቻል እንዳለበትም በመጠቆም የውጭ ባንኮች ጥቅም ይሰጣሉ ብቻ ሳይሆን ጉዳት የሚያስከትሉ መሆኑ መታሰብ ስላለበት ፖሊሲውን ለመተግበር ሥጋትን የሚቀንሱ መመርያዎች የሚያስፈልጉ መሆኑን ነው፡፡
እንደ አቶ እሸቱ እምነት የሚገቡት ባንኮች ለምሳሌ የኤክስፖርት ሥራ እንዲሠሩ መፈቀድ የለበትም፡፡ ምክንያቱም ባንኮች እየሠሩት ስለሆነ ይኼ ሥራ ከውጭ ባንኮች ከሥራ ዝርዝር ውስጥ መካተት እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ እሸቱ ምልከታ የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲከፈቱ አገር ውስጥ ሊያበድሩ የሚችሉትን ሀብት ማምጣት ያለባቸው መሆኑን ነው፡፡ በአገር ውስጥ ሀብት መጠቀም እንደሌለባቸው አመልክተዋል፡፡
የአገር ውስጥ ሀብትን ሰብስበው የሚያበድሩ ከሆነና በዚህ ሥራቸው በጣም ውጤታማ መሆን ቢችሉ እንኳን እንደ አገር የመጨረሻው ውጤት አገርን መጉዳት ነው ይላሉ፡፡
ስለዚህ እነዚህ ባንኮች የራሳችንን ሀብት ለብድር ማቅረብ አግባብ ስለማይሆን ይግቡ ከተባሉ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ሁሉ መታሰብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የባንኮቹ አከፋፈት ምን መሆን እንዳለበት በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ በቅደም ተከተል መተግበር የሚኖርበት መሆን እንዳለበት ያምናሉ፡፡
በየትኛውም መንገድ ቢገቡ ተቀማጭ ገንዘብ የማይወስዱና የውጭ ምንዛሪ ሥራዎች ላይ እንዲሠሩ የማይፈቀድላቸው መሆን አለበት፡፡
በአብዛኛው የገቢ ምርቶች ላይ የውጭ ምንዛሪ ማምጣታቸው ላይ ያተኮረ የባንክ ሥራ እንዲሠሩ ተደርጎ መመርያዎች መቀረፅ ይኖርባቸዋል የሚል ምክረ ሐሳብም ሰንዝረዋል፡፡
የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ የእነዚህ ባንኮች መግባት ጠቃሚ ጎን ያላቸው መሆኑን አስረድተው ሊያሳርፉ የሚችሉት ተፅዕኖ ግን በጥንቃቄ መታየት ይኖርበታል፡፡
ከዚህ ውጭ ግን አሁን የመንግሥት አቋም የሚያሳየው መግባታቸው የማይቀር በመሆኑ ‹‹ይግቡ አይግቡ›› የሚለው ጉዳይ ያበቃለት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳቱን ቀንሶ እንዴት ገብተው መሥራት እንደሚኖርባቸው በመነጋገርና እንዲህ ባሉ መድረኮች ላይ እየቀረቡ ያሉ ሐሳቦችን ብሔራዊ ባንክ በመመርያዎቹ እንዲያካትት መግፋት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የውጭ ባንኮች መግባታቸው አይቀርም ብለን ስንዘጋጅ ቆይተናል ያሉት የህብረት ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ከበደ በበኩላቸው ነገር ግን አገባቡ ደረጃ በደረጃ መግባት ያለባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አቶ መላኩ የባንኮቹ አገባብ መጀመርያ በሽርክና (በፓርትነርሺፕ) ቢጀመር ጠቃሚ እንደሚሆን ገልጸው፣ ከዚህ ልምድ በመነሳት ወደ ሌሎቹ አማራጮች መግባት ይቻላል ብለዋል፡፡ ሁሉንም አማራጮች በአንዴ መጠቀሙ ግን ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ፖሊሲው አይፈጸም የሚል ፍላጎት እንደሌላቸው የገለጹት አቶ እሸቱ ደግሞ ባለአክሲዮኖቻችን እንዳይጎዱ የውጭ ባንኮች አገባብ ደረጃ በደረጃ መሆን አለበት ይላሉ፡፡
እንደ ህንድና ሲሪላንካ ያሉ አገሮችም የውጭ ባንኮችን ያስገቡት ደረጃ በደረጃ በመሆኑ በፖሊሲ ስህተት አገርም ባንኮችን የፈጠሩ ባአክሲዮኖችም እንዳይጎዱ የውጭ ባንኮች አገባብ ደረጃ በደረጃ ሊሆን የሚገባ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ይህንን ሐሳብ የዕለቱ ተናጋሪዎች ሁሉም የተጋሩት ነበር፡፡
በዕለቱ ከተናጋሪዎቹም ሆነ ከተሳታፊዎቹ የተሰጡ በርካታ አስተያየቶች የተነሱ መሆናቸውን የገለጹት ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር) ይህ የሚያሳየው ፖሊሲው ሲወጣ ከኋላ ባዶ እንደሆነ ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ የቀረቡትን ሐሳቦች ግብዓት አድርጎ መንግሥት እንዲጠቀምበት ማደረግ ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የሕግ ባለሙያው ፈቃዱ ጴጥሮስ (ረዳት ፕሮፌሰር) ደግሞ ከሕግ አንፃር መታየት አለባቸው ያሉዋቸውን ሐሳቦች አቅርበዋል፡፡
በተለይ ለውጭ ባንኮች እስከ 30 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ እንዲሰጣቸው በረቂቅ ሕጉ ላይ የተቀመጠው አንቀፅ ለኢትዮጵያውያኖችም ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡ እስካሁን ያለው ሕግ አምስት በመቶ ብቻ የሚፈቅድ በመሆኑ ይህ ሕግ መስተካከል አለበት ብልዋል፡፡
ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ያሬድ ኃይለ መስቀል ደግሞ የውጭ ባንኮች መግባት ተግዳሮት ያለው ቢሆንም ገብተው እንዲሠሩ መፈቀዱ አግባብ እንደሆነና የኢትዮጵያ ባንኮችም ለዚህ ዝግጁ መሆን እንደሚገባቸው አመልክተዋል፡፡
የፓናል ውይይቱን የአዲስ ቻምበር ዋና ጸሃፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም የመሩት ሲሆን ንግድ ምክር ቤቱ ይህንን እና መሰል ጉዳዮችን ለፖሊሲ አውጪዎች እንደሚያቀርብ እና ለአድቮኬሲ እንደሚያውለው ተናግረዋል፡፡
post

ጥራትን መሰረት አድርጎ መሥራት የምርጫ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው! – ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ

ዘንድሮ ለ9ኛ ጊዜ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት በታላቁ ቤተመንግሥት ተከናውኗል።
ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ሽልማቱ ደረጃ ላይ ሳይንጠለጠል በጥራት መስፈርቶች ላይ መወሰኑ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
አክለውም እንደ ሀገር ለማደግ፣ የሕዝባችንን ኑሮ ለማሻሻል፣ ያለንን ራዕይ ለማሳካት ዛሬ ባለንበት ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ ካልሆንን፤ የመወዳደር አቅማችንን ካላጎለበትን፣ ምርቶቻችንን በዓይነትና በጥራት ለማቅረብ፣ በዓለም ገበያ ውስጥ ለመግባት ካልቻልን፣ በዚህ ሂደት ጥራት ማዕከላዊ ቦታ ይዞ ካልተገኘ ዕድገታችን ውሱን ይሆናል፤ ባለንበት እንድንዳክር ያደርገናል ብለዋል።
ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት፣ የሀገራችንን ራዕይ እውን ለማድረግ ጥራትን መሰረት አድርጎ መሥራት የምርጫ ብቻ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ ጥራት ያለው ምርት ለማምረትና አገልግሎት ለመስጠት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ሲሉ አሳስበዋል።
የጥራት ሽልማት ባልተለመደበት ሁኔታ ይህንን ተሞክሮ ይዘው በመምጣታቸው የጥራት ሽልማቱን ያዘጋጁ አካላትን አመስግነዋል።
በሽልማት መርሃ ግብሩ ላይ ከፍተኛ አድናቆት የተቸራቸው ሦስተኛና ሁለተኛ ደረጃ የጥራት ተሸላሚዎች ቢኖሩም አንደኛ ደረጃ ሽልማቱ ሳይሰጥ ተመልሷል።
ይህም የሆነው የጥራት ደረጃው የሚጠይቀውን መስፈርት ሊያሟላ የቻለ ተቋም ባለመገኘቱ ነው ተብሏል።
post

ንግድ ምክር ቤቱ የባንኩ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች መከፈቱን አስመልክቶ እየመከረ ነው

ጥቅምት 18/2015 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የባንኩ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች መከፈቱን በማስመልከት ምክክር እያካሄደ ይገኛል፡፡
በመድረኩ ላይ የባንኩ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች መከፈቱ ያለው ጥቅምና ተግዳሮቶች እንዲሁም የውጪና የሀገር ውስጥ ባንኮችን አዋህዶ መሄዱ ላይ ሊተኮርበት በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።
የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግ ባንኮች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዕድል ይፈጥራል የተባለ ሲሆን ብድርና ቴክኖሎጂዎችን በማስፋት የወጪና ገቢ ንግዱ እንዲሳለጥ ያግዛልም ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ውድድሩ ዓለም አቀፍ ልምዶችን ለመቅሰም ዕድል የሚፈጥርም ቢሆንም የመንግስትና ብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ድንገተኛና ጊዜውን የጠበቀ እንዳልሆነም ተነስቷል፡፡
ባንኮቹ ከመጡ በኋላ ምን አይነት ቁጥጥር መደረግ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ብሔራዊ ባንክ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርፆ መንቀሳቀስ አለበት ተብሏል።
የውጪ ባንኮቹ በመምጣታችው ሊከሰቱ የሚችሉ ተግዳሮቶችን በማጤን፣ በመገምገምና በሚያስገኙት ውጤት ላይ አተኩሮ መሰራት አለበት ተብሏል።
post

” ባለፉት በርካታ አስርት አመታት ሀገራችን በሯን ለውጭ የፋይናንስ ተቋማት ዝግ ማድረጓ ይታወቃል።

በእርግጥ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የፋይናንስ ዘርፉ በተለይም የባንክ ኢንዱስትሪው ለውጭ መከፈቱ አይቀሬ እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡
እኛም እንደ ንግድ ምክር ቤት የውጪ ባንኮች በሀገራችን የባንክ ዘርፍ ቢሳተፉ ከሚኖር ተግዳሮት ጎን ለጎን የሚገኙ እድሎችም እንዳሉ እንረዳለን፡፡
በተለይ ‹‹የግል ባንኮች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?፣ የሚኖረው የውድድር አውድ እስከምን ድረስ ነው? የሚለው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግሥት ይህንን ዕርምጃ ዕውን ማድረጉ ምን ጥቅም ያስገኛል? ምንስ ያሳጣል? የሚለው የአባሎቻችንም ሆነ የንግድ ምክርቤታችን ጥያቄ ይሆናል፡፡
በእርግጥ የውጭ ባንኮች በሀገራችን መግባታቸው ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጥርጥር ባይኖርም አገባባቸው ግን የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት ሁሉንም ያስማማል፡፡
ይህም አጠቃላይ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ከማሳደግና ለአገር ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር ታይቶ የሚወሰድ ዕርምጃ ይሆናል ብለንም እንገምታለን፡፡
የውጭ ባንኮች በሀገራችን የባንክ ዘርፍ መግባታቸው እርግጥ ከሆነ ‹‹አገባባቸው እንዴት ይሁን?›› የሚለው ጉዳይ የውይይታችን አንዱ አካል ይሆናል ፡፡ ለማንኛውም ራስን ማደርጀትና ጥሩ ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረብ፣ መትጋት፣ ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት ማድረግ፣ በሁሉም ረገድ ራስን ማደርጀትና ለውድድሩ ብቁ ማድረግ ለነገ የሚባል ባይሆን ይመረጣል”::
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የውጪ ባንኮች በሀገራችን የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንዲሰሩ መፈቀዱ ያለው እድልና ተግዳሮት በሚል የፓናል ውይይትን ለመክፈት ያደርጉት ንግግር
post

ኢትዮጵያ በሯን የከፈተችላቸው የውጭ ሀገር ባንኮች ኢትዮጵያ ሲገቡ የአገር ቤቶቹ ባንኮች የሚሰሩትን ስራ መድገም የለባቸው ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

ይመጣሉ ተብለው የሚጠበቁት ባንኮቹ በኢምፖርት እና ኤክስፖርት ስራ በፍፁም መሳተፍ የለባቸው ሲሉ የባንክ ፕሬዝዳንቶች ሲናገሩ ሰምተናል፡፡
ተህቦ ንጉሴ
ሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
post

A panel discussion is going on about the ” opening of the Domestic Banking Sector to Foreign Banks: Opportunities and Challenges”, organized by Addis chamber ,October 28, 2022, 8:30 AM Hilton Hotel .

Panelists
_ Ato Asfaw Alemu , CEO Dashen Bank
_Ato Melaku Kebede, CEO Hibret Bank
_Ato Eshetu Fantaye, CEO Ahadu Bank
_Prof Alemayehu Geda, Macro Economist AAU
_Ato Yared Hailemeskel, Investment Consultant
_Assistant Prof Fekadu Petros, Legal advisor
Key note speaker
– W/o Mesenbet Shenkute, President Addis Chamber
Moderator
_Ato Shibeshi Bettemariam, Secretary General, Addis Chamber
post

አዲስ ቻምበር የግሉን ዘርፍ በማጠናከር በሀገሪቱ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የበኩሉን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።

አዲስ ቻምበር ከሚያከናውናቸው ስራዎች መካከልም የግሉን ዘርፍ አበይት ጉዳዮችን በማንሳት ሀገራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማመቻቸት ነው።
እነዚህ የምክክር መድረኮች የግሉን ዘርፍና መንግስት ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሰሩ ከማድረጋቸውም በላይ ጠንካራና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ እንዲፈጠር የላቀ ሚና አላቸው።
የዚሁ አንድ አካል የሆነውና የውጪ ባንኮች በሀገራችን እንዲሰሩ መፈቀዱ ያለው እድልና ተግዳሮት / Opening of the Domestic Banking Sector to Foreign Banks: Opportunities and Challenges”. በሚል ርእስ ታላቅ የቢዝነስ ፓናል ውይይት አርብ ጥቅምት 18፣ ቀን 2015 ዓም ከ ጠዋቱ 2፡30 ሰአት ጀምሮ በሂልተን ሆቴል ተዘጋጅቷል፡፡
በመድረኩም ከመንግስት፣ከፋይናንስ ዘርፍ እና ከምሁራን የተለያዩ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
post

አዲስ ቻምበርና የኢፌዲሪ ፕላንና ልማት ሚንሰቴር በግሉ ዘርፍ ልማት ዙሪያ በጋራ መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መከሩ ፡፡

አዲስ ቻምበርና የኢፌዲሪ ፕላንና ልማት ሚንሰቴር በግሉ ዘርፍ ልማት ዙሪያ በጋራ መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መከሩ ፡፡
የአዲስ ቻምበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሽንቁጤና ዋና ፀሃፊው አቶ ሺበሺ ቤተማርያም ከክብርት የፕላንና ልማት ሚንስትር ፍፁም አሰፋ ( ዶ/ር ) ጋር ተወያይተዋል፡፡
መንግስት በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ ለግሉ ዘርፍ ትኩረት መሰጠቱን የጠቆሙት ዶ/ር ፍፁም ፤ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ ይበልጥ ተሳታፊ እንዲሆን ከአዲስ ቻምበር ጋር አብረን እንሰራለን ብለዋል ፡፡
ወ/ሮ መሰንበት ሽንቁጤ በበኩላቸው አዲስ ቻምበር በግሉ ዘርፍና በመንግስት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር ድልድይ ሆኖ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል ፡፡
ሁለቱ ተቋማት በቀጣይ በግሉ ዘርፍ እድገት ላይና መሰል የኢኮኖሚ ልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡