የጋራ ስምምነቱ የንግዱን ህብረተሰብ እና የምክር ቤቱን አባላት እንዲሁም ምክር ቤቱን በላቀ ሁኔታ እንዲጠቅም ተደርጎ የሚተገበር ነው ተብሏል።
ምክር ቤቱን በመወከል ስምምነቱን የተፈራረሙት የምክር ቤቱ ፕረዚደንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ ናቸው፡፡ የገዳ ባንክን በመወከል የተፈራረሙት ደግሞ የባንኩ ፕረዚደንት አቶ ወልዴ ቡልቶ ናቸው፡፡
ከመግባቢያ ስምምነቱ ጋር በተያያዘ በሁለቱ ተቋማት መሪዎች አማካኝነት ገንቢ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ምክር ቤቱ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ የጸና ንግድ ፍቃድ ያላቸውና በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ ወኪልና ድምጽ እንደመሆኑ መጠን እንዲህ አይነት ስምምነቶች ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲበረታታ፤ የገቢና ወጪ ንግድ እንዲያድግ፤ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዜጎች በሀገር ውስጥ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት በማገዝ እንዲሁም ለንግዱ ማህበረሰብ የገንዘብ አቅርቦት እንዲመቻች የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል የምክር ቤቱ ፕረዚደንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ፡፡
ገዳ ባንክ አዳዲስ ከተመሰረቱት ባንኮች መካከል አንዱ ነው ያሉት የባንኩ ፕረዚደንት አቶ ወልዴ ቡልቶ ባንካቸው ከዘላቂ ልማትና ከካፒታል ኢኮኖሚ ጋር አብሮ የሚሄድ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከስምምነቱ ጋር በተያያዘ በተለይም አነስተኛና ጀማሪ የቢዝነስ ተቋማትን ተጠቃሚ ለማድረግ፤ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋት፤ ከወለድ ነጻ የብድር አገልግሎት፤ አሁን በስራ ላይ ያለው የክሬዲት ወሰን እንዲሻሻል ከአዲስ ቻምበር ጋር በአድቮኬሲ ጉዳዮች ፤በስልጠናና አቅም ግንባታ ዙርያ በጋራ እንደሚሰሩ የባንኩ ፕረዚደንት አክለው ተናግረዋል፡፡
ስምምነቱ ከፊርማ ባለፈ ወደ ተግባር ለመቀየር መስራት እንዳለባቸው የሁለቱ ተቋማት መሪዎች እና ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተስማምተዋል፡፡
