ለሶስት ተከታታይ ቀን በአዲስ አበባ ኢግዚቢሽን ማእከል ሲካሄድ የነበረው እና በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ የሃገር ውስጥ እና የውጭ ሃገር ነጋዴዎችን ያሳተፈው 27ተኛው አዲስ ቻምበር አለም አቀፍ ንግድ ትርኢት የውጭ ንግድ በተለይም የቡና ዘርፍ ተወዳዳሪነት ላይ ትኩረት ባደረገ ሲምፖዚየም ተጠናቋል፡፡
በሲምፖዚየሙ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ መሃመድ ፡የቦርድ አባላት፡ በንግድ ትርኢቱ የተሳተፉ ነጋዴዎች እንዲሁም ባለድርሻዎች ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛት ወርቁ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፡የቡና የወጭ ንግድ ተወዳዳሪነትን እንዴት ማገዝ ይቻላል ያሉት ክፍተቶችስ ምንድንናው በሚል ባቀረቡት ሃሳብ ላይ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ የቡና አይነቶች በአለም ተወዳዳሪ ሊያርጉን እንደሚችሉ ጠቁመው እነዚህ ላይ የማስተዋወቅ ስራ ቢሰራ የመሸጥ አቅምን መጨመር እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ቡና ቆልቶ ለአለም ገበያ ከማቅረቡ በተጨማሪ አረንጓዴውን ቡና በተሻለ ጥራት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ተወዳዳሪነትን እንደሚጨምር ገልጸዋል፡፡
ዘርፉ ላይ ከሚታዩ እና ተወዳዳሪነትን ከሚቀንሱት ክፍተቶች መካከል ተቋማዊ አሰራሩ ወደ አንድ መምጣቱ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም የፖሊሲ ድጋፍን አስመልክቶ የገበያውን ተለዋዋጭነት ከግምት ያስገባ አለመሆኑ፡የቡናን ገበያ አስመልክቶ መረጃ መሰብሰብ ላይ እንዲሁም ማሸግያ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ካነሷቸው ተወዳዳሪነትን ከሚቀንሱት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በሲምፖዚየሙ የቀረበውን የውይይት መነሻ ተከትሎ ሃሳብ አስተያየት እንዲሁም ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች የተነሱ ሲሆን ምላሽ እና ማብራርያ ተሰቶባቸዋል፡፡
በመጨረሻም ለ27ኛው የአዲስ ቻምበር አለም አቀፍ ንግድ ትርኢት መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት እና አጋር ድርጅቶች የምስጋና እና የእውቅና ሽልማት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ መሃመድ በማበርከት የማጠቃለያ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡
