ጠንካራና ቀጣይነት ያለው ማክሮ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጤናማ፣ ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋ እና ሊተነበይ የሚችል የግብር ስርአት መኖር ወሣኝ መሆኑን የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ተናግረዋል ።
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) “የታክስ አስተዳደር ለውጦች ፣ እድሎች፣ ተግዳሮቶችና ምርጥ ተሞክሮዎች” በሚል ርዕስ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት 5ኛውን የግሉና የመንግስት የጋራ የምክክር መድረክ አካሂዷል ።
(ሠኔ 25፤ 2018 ፤ አዲስ ቻምበር)
የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከተቋቋመባቸው አላማዎች አንዱ የፖሊሲ አድቮኬሲ ስራዎችን በማካሄድ ለንግድና ኢንቨስትመንት አስቻይ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ማድረግ ነው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ምክር ቤቱ ባለፉት ጥቂት ጊዜያት በርካታ የምክክር መድረኮችን በማመቻቸት ቁልፍ ባለ ድርሻ አካላት እንዲመክሩና የተሻሉ የንግድ ህጎችና ፖሊሲዎች እንዲወጡና እንዲተገበሩ ከፍተኛ ሚናን ተጫውቷል፡፡
የዚህ አንድ አካል የሆነው 5ኛው የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ከአለም አቀፉ የግል ኢንተርፕራይዝ ማእከል(ሳይፕ) ጋር በመተባበር በታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ፣ ለውጦች፣ተግዳሮቶችና መልካም ተምክሮዎች ዙርያ ትኩረቱን በማድረግ በኢንተርላግዠሪ ሆቴል ተካሂዷል።
የምክክር መድረኩ የሚመለከታቸው የገንዘብ ሚኒስቴርና ሐላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ገቢዎች፣ የከተማዋ የንግድ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ቢሮ አመራሮች ፣የአዲስ ቻምበር ከፍተኛ አመራሮች፣ጥናት አቅራቢዎች ፣የንግዱ ማህበረሰብ አባላት እንዲሁም ቁልፍ ባለ ድርሻ አካላትን በማገናኘት በግብር ስርአት፣ አስተዳደርና አተገባበር ዙርያ ሰፊ ሃሳቦች የተንሸራሸሩበት መድረክ ነበር፡፡
በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሐላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ እንደተናገሩት ቢሮው የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ ዘርፈ ብዙ የሪፎርምና የለውጥ ስራዎች መስራቱን ጠቅሰው መስሪያ ቤታቸው ለንግዱ ህብረተሰብ የሚሰጠውን አገልግሎት እጅግ ቀላል፣ ፈጣንና ዘመናዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት ርብርብ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።
የግሉ ዘርፍ በግብር ጉዳይ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች በአዲስ ቻምበር በኩልና በተደራጀ መልኩ እየፈታ መሆኑን የቢሮ ሐላፊው አስረድተዋል ።
የአዲስ ቻምበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሐራ መሐመድ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው የግብር አስተዳደርና አተገባበር ጉዳይ ዋነኛው የግሉ ዘርፍ ተግዳሮት መሆኑን ተናግረው እንዲህ አይነት ችግሮችን ለመፍታት ምክር ቤታቸው ወሳኝ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ፤ የፖሊሲ ግብአቶች የሚሰበሰቡበትና አመቺ ፖሊሲዎች እንዲወጡና ተግባራዊ እንዲደረጉ ምክር ቤቱ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የአዲስ ቻምበር አባል ኩባንያዎችና መላው የንግዱ ማህበረሰብ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ውስጥ የሚጫወቱት ሚና እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ በማስታወስ ጠንካራና ቀጣይነት ያለው ማክሮ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጤናማ፣ ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋ እና ሊተነበይ የሚችል የግብር ስርአት መኖር ወሣኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ለውይይት የሚሆኑ ጹሁፎች ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ፣ ከከተማዋ ገቢዎች መማክርት ጉባኤና ከግሉ ዘርፍ በሚመለከታቸው ሀላፊዎችና ባለሙያዎች የቀረቡ ሲሆን ሰፋ ያሉ ሀሳቦችና ግብአቶች ቀርበውበታል፡፡
ከተነሱ ሀሳቦችና ምልከታዎች መካከል
ተሻሽሎ ስራ ላይ መዋል የጀመረው የፌዴራል ገቢ ግብር አዋጅ ነባራዊ ሁኔታዎችን ማገናዘብ እንደነበረበትና አንዳንድ ጥብቅ ድንጋጌዎችም ያሉበት መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን ይህም ድርጅቶች ቢከስሩ እንኳን ከዓመታዊ ሽያጫቸው 2.5 በመቶ ግብር መክፈል አለባቸው የሚለው አንዱ ድንጋጌ የግሉ ዘርፍ የሚያነሳው ጉዳይ መሆኑ ተጠቅሷል።
በተለይ ከፍተኛ ሽያጭ ያላቸው ግን ደግሞ የትርፍ ህዳጋቸው አነስተኛ የሆኑ እንደ ማኑፋክቸሪንግ እና ጅምላ ንግድ ያሉ ዘርፎች በዚህ ረገድ ሊጎዱ እንደሚችሉ በምክክሩ ወቅት ተመላክቷል።
የደረጃ ሀ እና ለ ታክስ ከፋዮች በየሶስት ወሩ የቅድሚያ ግብር መክፈል አለባቸው የሚለው የአዋጁ ድንጋጌም በብድርና በብድር ጭምር የሚሰሩ ነጋዴዎችን ላልተገባ ጫና ይዳርጋል የሚል ስጋት በምክክሩ ሀሳብ ተሠንዝሯል።
በአጠቃላይ የታክስ አስተዳደር ሪፎርም አሠራርና አተገባበር በግሉ ዘርፍ ላይ ያለው አንድምታ በሚል የተካሄደው የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ከንግዱ ማህበረሰብና ከሚመለከታቸው ሀላፊዎች በርካታ ምላሾችና ምክር ሀሳቦች የተዳሰሱበት ሲሆን በተለይ የታክስ አሠራር እና አተገባበር ቀልጣፋና ለንግድ አሰራር አስቻይ እንዲሆን አሁን ያለው ፖሊሲ፣ ሕግና መመሪያ ወደፊት ከሚታሰበው የግል ዘርፉ ሚና አኳያ መቃኘት እንዳለበት፤ ለውጡን በአግባቡ ለመተግበር የሚያስችሉ ብቁ ተቋማትና የሠው ሐይል፤ ወጥ ስትራቴጂና ዝርዝር ህጎች በስራ ላይ ማዋል ፤ በታክስ አሰባሰብ ሂደት ውስጥ ቴክኖሎጂን መጠቀም፤ ፍትኃዊና ተጠያቂነት ያለበት የታክስ ስርአትን መፍጠርና ግንዛቤ እንዲያድግ ማድረግ የሚሉት በፓናል ውይይቱ የተነሡ ነጥቦች ናቸው ፡፡
በመጨረሻም በምክክር መድረኩ መፈታት አለባቸው የተባሉ ተግዳሮቶችን በማጠናቀር ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላትና ለገቢ ሠብሳቢ መስሪያ ቤቱ በማቅረብ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ክትትል እንደሚደረግ አዲስ ቻምበር ገልጿል፡፡
አዲስ ቻምበር በቀጣይም በተለያዩ ዋነኛ የፖሊሲ አድቮኬሲ ጉዳዬች ዙሪያ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረኮች በተከታታይ እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል ።
#advocacy #policyadvocacy
#addischamber
