የንግድ ማህበረሰቡ ከባንኩ ያለ ማስያዣ ከ60 ሺህ ብር እስከ 1 ሚሊየን ብር የሚደርስ ብድር ማግኘት እንደሚችል ተጠቁሟል
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) ከዘምዘም ባንክ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል። የዚህ ስምምነት ዋና ዓላማ የባንኩን ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎቶች ለንግዱ ማህበረሰብ በተለይም ለአነስተኛና መካከለኛ ነጋዴዎች ተደራሽ ማድረግ ነው።
ይህንን ስምምነት ያደረጉት የአዲስ ቻምበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ወ/ሮ ዘሐራ መሐመድ እና የዘምዘም ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ መሊካ በድሪ ናቸው።
እንደ ስምምነቱ ከሆነ ፤ ባንኩ በአገልግሎቱ ላይ ዲጂታል ቴክኖሎጂን እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የተደገፈ የብድር አሰጣጥ ስርዓትን በመጠቀም ከማስያዣ ነፃ የሆኑ የፋይናንስ አማራጮችን ለንግዱ ማህበረሰብ ያቀርባል።
ከዚህ በተጨማሪም ፤ የንግድ ማህበረሰብ ከባንኩ ያለ ማስያዣ ከ60 ሺህ ብር እስከ 1 ሚሊየን ብር የሚደርስ ብድር ማግኘት እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
በስምምነቱ ወቅት እንደተገለፀዉ ፤ ምክር ቤቱ እና ባንኩ የንግዱን ማህበረሰብ ችግሮች በመለየት ተገቢውን የፋይናንስ መፍትሄ ለመስጠት በጋራ እንደሚሰሩ ታውቋል።
አዲስ ቻምበር
