ንግድ ም/ቤቱ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ጂዲታል ሊያሸጋገር ነው

ከወረቀት ነጻ የሆነ ቨርቿል ሥርዓት (ERP) በአዲሱ አመት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በይድነቃቸው ዓለማየሁ
አዲስ ቻምበር ለአባላቱ የሚሰጣቸውን ነባር አገልግሎቶች በይበልጥ ቀልጣፋ እና ተደራሽ ለማድረግ ፤እንዲሁም ዘመኑ የሚጠይቀውን አዳዲስ የቻምበር አገልግሎቶች ለንግዱ ሕብረተሰብ በስፋት ለማድረስ በዛሬው ዕለት በንግድ ምክር ቤቱ እና ኤክሲድ በተባለ አማካሪ ድርጅት መካከል የ ERP የሥራ ስምምነት ውል ተፈርሟል፡፡
ERP-ኤንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ የአንድን ተቋም ፤ግንኙነቶች እና የሚሰጣቸውን አገልግሎቶችን ወደ ጂጂታል ሥርዓት የሚያሸጋግር ቴክኖሎጂ ሥርዓት አንደማለት ነው፡፡
በሥነ ስርዓቱ ላይ የአዲስ ቻምበር ዋና ፀሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም የ ERP ሥራ መጀመር እንደ አድቮከሲ፤ሥልጠና ፤ የግልግል ዳኝነት፤ የኮሚኒኬሽን ፤ዳይሬክተሮች ኢንሰቲቲዩት እና የሥራ መሪዎች መድረክ በመሳሰሰሉት አዳዲስ አገልግሎቶችን በቨርቿል ቴክኖሎጂ በቀላሉ በዓለም ዙሪያ ተደራሽ ማድረግ ያስችለል ብለዋል፡፡
ሽግግሩ በንግድ ም/ቤቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ታሪክ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ፕሮጀክት መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኤክሲድ ኩባንያ ኃላፊዎች በበኩላቸው የሚጀመረው የ ERP ቨርቿል ቴክኖሎጂ ሥርዓት በተጨማሪም የአዲስ ቻምበር የውስጥ አሰራሮች ላይ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ለማስፈን፤ የሰው ኃይል ፤ሃብት እና ጊዜ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ሥራዎችን ለማከናወን ይረዳል ብለዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ትግበራ ላይ የማኔጅመነት አባላት እና ሠራተኞችን እንደሚሳተፉ እና ሥልጠና አንደሚሰጣቸው ገልጸዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ይፋዊ ማስጀመሪያ ሥነሥርዓትም በቅርቡ አንደሚካሄድ እና ሙሉ በሙሉ የዲጂታል ሽግግሩ መጀመር በአዲሱ አመት አንደሚጠበቅ ለመረዳት ተችሏል፡፡