የቴክኒክና ሙያ ስልጠናን ለማጠናከርና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ተገመገመ 

በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ላይ ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙት የ DESTA (Digital Ethiopia skills and TVT Action) እና የ ስቴፕ (STEP IV) ፕሮጀክቶች የሥራ አፈጻጸምና የቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የስትሪንግ ኮሚቴ ውይይትና ግምገማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው፤ እነዚህ ፕሮጀክቶች በክህሎት ልማት ፣ በቴክኒክና ሙያ ፖሊሲና ስትራቴጂ ዝግጅት፣ በአረንጓዴ ቴክኒክና ሙያ (Green TVT) እና በዲጂታላይዜሽን ረገድ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።

በተጨማሪም በሥልጠና ሰነድ ዝግጅት፣ በሥርዓተ ጾታ እኩልነትና አካታችነት፣ እንዲሁም በግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማረጋገጥ ዙሪያ በመንግስት የሚሰሩ ሥራዎችን በማገዝ ላይ ናቸው። ፕሮጀክቶቹ በሀገሪቱ የክህሎት ልማትና አካታችነት ላይ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ መሆኑ በመድረኩ ተመላክቷል።

ይህ የጋራ መድረክ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ጥራትን በከፍተኛ ደረጃ ለማሻሻል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አፈጻጸም ለመገምገም የተዘጋጀ ሲሆን፤ በሂደቱ የታዩ ክፍተቶችን በማረምና የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ወደ ሥራ ለመግባት የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።

በዚሁ የምክክርና የሥራ ግምገማ መድረክ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) ጨምሮ የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች፣ የጀርመን ልማት ድርጅትና የፊንላንድ ተወካዮች እንዲሁም አዲስ ቻምበርን ጨምሮ የግሉ ሴክተር ተወካዮች ተሳትፈዋል።

wpChatIcon
wpChatIcon