የሴቶች የአመራር አቅምን ማሳደግ የሚያስችል ስልጠና ተሰጠ::

ሴቶች ወደአመራርነት እንዲመጡ በተቋማት ውስጥ ምቹ ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚገባ ተጠቅሷል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የዳይረክተሮች ተቋም ያዘጋጀው ስልጠና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የአመራርነት ልምድ ባላቸው በወ/ሮ ሂክመት አብደላ እና በሌሎች ባለሞያዎች ተሰጥቷል፡፡
ስልጠናውን በተለያዩ ተቋማት በአመራርነት እንዲሁም በቦርድ ውስጥ የመስራት እድሉን ያገኙ ሴቶች ተሳትፈውበታል፡፡
በአመራርነት ቦታ ያሉ ሴቶች የሚገጥሟቸው ችግሮች በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሚፈጥሩት ተጽኖ እንዲሁም ጾታ ተኮር ፍረጃ ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡
በአመራርም ሆነ በሌሎች ስራዎች ላይ ያሉ ሴቶች ስራዎቻቸው ላይ በማተኮር ወደ አመራርነት እንዳይደርሱ ተቋማት የሚሞክሩበትን እድል የማይሰጡ እና በስልጠና እና በትምህርት ሊሞሉ የሚችሉ ክፍተቶችን በቀጥታ ከጾታ ጋር በማያያዝ ወደኋላ የሚያስቀሩ አሰራሮችን ሲከተሉ የቆዩ መሆናቸው ለሴቶች ወደ አመራርነት መምጣት እንቅፋት እንደነበሩ ወ/ሮ መሊካ በድር የዘምዘም ባንክ ዋና ስራ አስኪያጅ ልምዳቸውን ባካፈሉበት ወቅት ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ተቋም የአመራሮችን አቅም ለማጎልበት የሚያግዙ ተከታታይ ስልጠናዎችን የሚሰጥ ሲሆን የሴቶችን የአመራር አቅም ለማጎልበት የሚሰጡ ስልጠናዎች ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው ተብሏል፡፡
በምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ተቋም በተዘጋጀው ስልጠና ሴቶች የአመራርነት አቅማቸውን ማሳደግ እንዲችሉ የሚረዱ የልምድ ልውውጦች፡የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን እንዲሁም አመራርነትን እና ሌሎች ሃላፊነቶችን አመጣጥኖ መሄድ የሚችሉበትን መንገድ የሚጠቁሙ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡
በስልጠናው ንግድ ምክር ቤቱ እንደሃገር ያለውን ክፍተት በመረዳት የዳይረክተሮች ተቋምን ማቋቋሙ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ወ/ሮ ሂክመት ከቦርድ ጋር የተያያዙ የአመራር ክህሎቶችን ለማዳበር እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
በምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ተቋምም የሴቶችን የአመራር አቅም የሚገነቡ ስልጠናዎች በቀጣይ እንደሚካሄዱ ታውቋል፡፡