የለሚ ኩራ ክ/ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት በየወሩ ከነጋዴዎች፤ከመማክርት ጉባዔ እና ከሌሎች ባለደርሻዎች ጋር በተገልጋዮች እርካታና በአግልግሎት አሰጣጥ ላይ መደበኛ ውይይት ያካሂዳል፡፡ ግብር ከፋዩ ሕ/ሰብ ክብር አግኝቶ ግዴታውን በታማኝነት እንዲወጣ የከተማው አሰተዳደር የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን የክ/ከተማው ገቢዎች ጽ/ቤት ም/ሥራአስኪያጅ አቶ ሃይሉ ተስፋዬ ገለጸዋል፡፡
ከግብር ከፋዩ ሕ/ሰብ አብላጫውን ቁጥር የሚይዘው የንግዱ ሕ/ሰብ ነው፡፡ ነገር ግን ነጋዴው በግብር ሥርዓቱ ላይ በሚሰተዋሉ እንደ ሙስና እና አድሎአዊ አሰራሮች ችግር ሲደረስበት መቆየቱን አስታውሰው ነገር ግን ከቅርብ አመታት ወዲህ መንግሥት በጀመረው የዲጂታላይዜሽን ሪፍርም አማካኝነት ከሰው ንክኪ ነጻ አንዲሆኑ ከተደረጉት መንግሥታዊ አገልግሎቶች መካከል አንዱ የታክስ ሥርዓቱ ነው ብለዋል፡፡
ዛሬ ላይ ነጋዴው ካለበት ቦታ ሆኖ አመታዊ ሽያጩን ማሳወቅ፣ከሊራንስ መውሰድ፤የግብርና ሌሎች ክፍያዎችን መፈጸም የሚያስችለው የኦንላይን ሥርአት ተጠቃሚ እየሆነ ነው ብለዋል፡፡ ጽ/ቤታቸውም የግብር ሥርዓቱ ላይ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ነጋዴዎችን ጨምሮ ከሁሉም ባለድርሻዎች ጋር በሚያደርጋቸው ወርሃዊ የጋራ ውይይቶች አማካኝነት በተገልጋይ ላይ የሚደርሱ በደሎችን በአፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ በመቻሉ መልካም ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡ በተለይ በቅርቡ የገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች በሥራ ሰዓት ተገልጋይን አስቀምጠው ስልክ የመጠቀም ክልከላ አደርጓል፡፡ ይህም ለግብር ከፋዩ ተገቢውን ክብር ለመስጠት ነው፡፡ ቢሆንም በቀጣይ ነጋዴው የሚያቀርባቸውን ቅሬታዎች በጋራ እየፈታን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ከነጋዴዎች ቅሬታዎች ተነስተዋል፡፡ ከነዚህ መካከል አልፎ አልፎ ረዣዥም ወረፋዎች መኖር፤ የክፍያ ማረጋገጫ መልእክት በስልክ አይደርሰንም፤ በገቢዎች ሰራተኞች መካከል ወጥ የሆነ መረጃ የለም የሚሉት ይገኝባቸዋል፡፡ ሥ/አስኪያጁ በበኩላቸው የቀረቡ ቅሬታዎችን ተቀብለው የሚመለከታቸውን የሥራ ክፍሎችን በማነጋገር መፍትሄ እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል፡፡
የአዲስ ቻምበር የለሚ ኩራ ቅርንጫፍ ዋና አስተባባሪ እና የመማክርት ጉባዔው ስብሳቢ አቶ መሐመድ ሙስጠፋ ጉባዔው ከጽ/ቤቱ ጋር በጋራ እየሰራ የነጋዴዎችን ቅሬታዎች እየፈታ ነው ብለዋል፡፡ ይህም በነጋዴውና በመንግሥት መካከል መተማመን እንዲኖር ይረዳል፡፡ ቅ/ጽቤቱ ነጋዴዎች የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች ከክ/ከተማው ሃላፊዎች ዘንድ በማድረስ ኢፍትሀዊ ወሳኔዎች ተቀልብሰው በርካታ ነጋዴዎች ፍትሕ እንዲያገኙ መደረጉን ትናግረዋል፡፡ ነገር ግን የንግዱ ሕ/ሰብ መብቱን በተሻለ ሁኔታ ማስክበር የሚችለው የአዲስ ቻምበር አባል በመሆን እንደሆነ ገልጸው ነጋዴዎች በቻምበሩ አባልነት እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አዲስ ቻምበር የግሉ ዘርፍ ድምጽ!
