የአሜሪካን ማእከላዊ ባንክ ምክትል ሀላፊና የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ምክትል ረዳት ፀሀፊ ኤሪክ ሜየር በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝታቸው ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት(አዲስ ቻምበር) ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በኢትዮጵያ የቢዝነስ ከባቢ ሁኔታ እና የግሉ ዘርፍ ልማት ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ሁለቱም ወገኖች በሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በእነዚህ ውጥኖች የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትና የንግዱ ማህበረሰብ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል።
ሚስተር ኤሪክ ሜየር የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም እያካሄደ ያለውን ማሻሻያ በማድነቅ የአገልግሎት ዘርፉ በተለይም የባንክ እና የቴሌኮሙኒኬሽን ለውጭ ባለሀብቶች መከፈት እንዲሁም የአክሲዮን እና የካፒታል ገበያን መጀመር እንደ አንድ ጥሩ ምሳሌ ጠቅሰዋል፡፡
የኢኮኖሚ መዋቅሩ “ከመንግስት ወደ ግሉ ዘርፍ መር ኢኮኖሚ መሸጋገር ትልቅ ስራ ነው ያሉት ኃላፊው እነዚህን ማሻሻያዎች መንግስትና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ እና ያሉባቸውን ክፍተቶች በማስተካከል ውጤታማነታቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
የግምጃ ቤት ሀላፊው እንደተናገሩት ውጭ ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ውስጥ የሚላከው ገንዘብ ለግሉ ዘርፍ እድገትና ለንግድና ኢንቨስትመንት ልማት ቁልፍ ሚና እንዳለው የገለጹ ሲሆን በኢትዮጵያ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን የበለጠ የሚያጎለብት የመንግስትና የግል ዘርፍ አጋርነት አሰራር እና ውይይት እንዲጎለብት የበለጠ የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግም ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።
የአዲስ ቻምበር ዋና ፀሐፊ አቶ ዘካርያስ አሠፋና ሌሎች አመራሮች ሀላፊዎችን ተቀብለው ያነጋገሩ ሲሆን አዲስ ቻምበር የግሉ ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆንና ምቹ የቢዝነስ ምህዳር እንዲፈጠር የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሆነ ለልኡካን ቡድኑ አስረድተዋል።
አንጋፋው አዲስ ቻምበር የግሉ ዘርፍ ልማት እንዲረጋገጥ የተለያዩ በመረጃ የተደገፉ ምክረ ሐሳቦችን ለመንግስት በማቅረብ የሚታወቅ ሲሆን በዋና ዋና ትኩረት በሚሻቸው የንግዱ ማህበረሰብ ጉዳዮች ዙሪያ የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ እያዘጋጀ መሆኑንም ተመልክቷል ።
