በታክስ እና ጉምሩክ ዙርያ የሚወጡ ህጎችና አሰራሮች ፍትሀዊ፣ግልፅና የሚተነበዩ እንዲሆኑ ተጠየቀ።

የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከተቋቋመባቸው አላማዎች አንዱ የፖሊሲ አድቮኬሲ ስራዎችን በማካሄድ ለንግድና ኢንቨስትመንት አስቻይ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ማድረግ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ምክር ቤቱ ባለፉት ጊዜያት በርካታ የምክክር መድረኮችን በማመቻቸት ቁልፍ ባለ ድርሻ አካላት እንዲመክሩና የተሻሉ የንግድ ህጎችና ፖሊሲዎች እንዲወጡና እንዲተገበሩ ከፍተኛ ሚናን ተጫውቷል፡፡

የዚህ አንድ አካል የሆነው የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ በታክስና ጉምሩክ ሪፎርም ፣ ትግበራና ተግዳሮቶች ዙርያ ትኩረቱን በማድረግ ተካሂዷል፡፡

“የታክስ እና የጉምሩክ ሪፎርም አተገባበር በግሉ ዘርፍ ላይ ያለው ተጽእኖ” በሚል ርእሰ ጉዳይ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የመጀመሪያው የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ አዲስ ቻምበር ከአሜሪካን ንግድ ምክር ቤት በኢትዮጲያ እና ከአለም አቀፉ የግል ኢንተርፕራይዞች ማእከል ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ተካሂዷል።

የምክክር መድረኩ የሚመለከታቸው የገንዘብ ና የገቢዎች ሚኒስቴር ሀላፊዎች ፣ የጉምሩክ ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አመራሮች ፣ የአዲስ ቻምበር እና የአሜሪካን ንግድ ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች፣ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት እንዲሁም ቁልፍ ባለ ድርሻ አካላትን በማገናኘት በግብር እና በጉምሩክ ስርአት፣ አስተዳደርና አተገባበር ዙርያ ሰፊ ሃሳቦች የተንሸራሸሩበት መድረክ ነበር፡፡

በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ አለምወርቅ ደረሰ እንደተናገሩት ኮሚሽኑ የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ ዘርፈ ብዙ የሪፎርምና የለውጥ ስራዎች መስራቱን ጠቅሰው መስሪያ ቤታቸው ለንግዱ ህብረተሰብ የሚሰጠውን አገልግሎት እጅግ ቀላል፣ ፈጣንና ዘመናዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት ርብርብ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

የግሉ ዘርፍ የሚያነሳቸውን ተግዳሮቶችም በተደራጀ እና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ተቀራርቦ ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ጠቁመዋል ።

የአዲስ ቻምበር ዋና ጸሀፊ መሠረት ሞላ (ዶ/ር) በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው የግብር እና የጉምሩክ ጉዳይ ከበርካታ አመታት ጀምሮ ሲንከባለል የመጣ ችግር መሆኑን ተናግረው እንዲህ አይነት ችግሮችን ለመፍታት ምክር ቤታቸው ወሳኝ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ፤ የፖሊሲ ግብአቶች የሚሰበሰቡበትና አመቺ ፖሊሲዎች እንዲወጡና ተግባራዊ እንዲደረጉ ምክር ቤቱ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የአሜሪካን ንግድ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ናትናኤል መላኩ እንደተናገሩት አባል ኩባንዎቻቸውና መላው የንግዱ ማህበረሰብ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ውስጥ የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ በማስታወስ ጠንካራና ቀጣይነት ያለው ማክሮ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጤናማ፣ ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋ እና ሊተነበይ የሚችል የግብር እና የጉምሩክ ስርአት መኖር ወሣኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ለውይይት የሚሆኑ ጹሁፎች ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር ፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን እና አግሉ ዘርፍ በሚመለከታቸው ሀላፊዎችና ባለሙያዎች የቀረቡ ሲሆን ሰፋ ያሉ ሀሳቦችና ግብአቶች ቀርበውበታል፡፡

ከተነሱ ሀሳቦችና ምልከታዎች መካከል የኢትዮጵያ የታክስ ምጣኔ ከጥቅል አመታዊ ምርት ጋር ሲነጻጸር ከአመት አመት እየቀነሠ መምጣቱ፤ የታክስ እና ጉምሩክ ሪፎርሞች ከተቋማት ብቃትና ፤ከሰለጠነ የሰው ሀይል አንጻር ክፍተቶች እንዳሉበት፤ የታክስ እና ጉምሩክ አስተዳደርና አተገባበሮች ኢንቨስትመንትን የሚያበረታቱ አለመሆናቸው፤ የታክስ ፖሊሲ ለውጦችን በየጊዜው ከሚለዋወጠው ኢኮኖሚ ጋር በማነጻጸር ለውጥ ያለማድረግ ክፍተቶች መሆናቸውን በዋናነት ተጠቅሰዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ በምክክር መድረኩ  ከተነሱት ሀሳቦች መካከል የቅንጅታዊ አሰራር መጓደል፤  የታክስ ከፋዮችን መብት ሊያስከብር የሚችል ነፃና ገለልተኛ ተቋም አለመኖር፤ የታክስ ግጭት አፈታት ረጅምና አሰልቺ መሆን በዋናነት ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡

በግብር ይግባኝ ችሎት በቂ የግሉ ዘርፍ ተወካይ እንዲኖርና በግብር ይግባኝ ክርክር ወቅት ቅድሚያ የሚከፈለው የ 50 በመቶ መጠን ወደ 20 በመቶ ዝቅ እንዲል እንደ ምክረ ሀሳብ ተጠይቋል ።

በአጠቃላይ “የታክስ እና የጉምሩክ ሪፎርም አሠራርና አተገባበር በግሉ ዘርፍ ላይ ያለው አንድምታ” በሚል የተካሄደው የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ከንግዱ ማህበረሰብና ከሚመለከታቸው ሀላፊዎች በርካታ ምላሾችና ምክር ሀሳቦች የተዳሰሱበት ሲሆን በተለይ የኢትዮጵያ የታክስ እና ጉምሩክ አሠራር እና አተገባበር ቀልጣፋና ለንግድ አሰራር አስቻይ እንዲሆን አሁን ያለው ፖሊሲ፣ ሕግና መመሪያ ወደፊት ከሚታሰበው የግል ዘርፉ ሚና አኳያ መቃኘት እንዳለበት፤ ሪፎርሞቹን በአግባቡ ለመተግበር የሚያስችሉ ብቁ ተቋማት፤ ወጥ ስትራቴጂና ዝርዝር ህጎች በስራ ላይ ማዋል ፤ በታክስ አሰባሰብ ሂደት ውስጥ ቴክኖሎጂን መጠቀም፤ ፍትኃዊና ተጠያቂነት ያለበት የታክስና ጉምሩክ ስርአትን መፍጠርና ግንዛቤ  እንዲያድግ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል ፡፡

በመጨረሻም በምክክር መድረኩ መፈታት አለባቸው የተባሉ ተግዳሮቶችን በማጠናቀር ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በማቅረብ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ክትትል እንደሚደረግ አዲስ ቻምበር  ገልጿል፡፡

አዲስ ቻምበር በቀጣይም ከአሜሪካን ንግድ ምክር ቤት በኢትዮጵያና ከአለም አቀፉ የግል ኢንተርፕራይዞች ማእከል ጋር በመተባበር በተለያዩ የፖሊሲ አድቮኬሲ ጉዳዬች ዙሪያ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረኮች በተከታታይ እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል ።