የአዲስ ቻምበር የንግድ ልኡክ በቤልጅየም እና ሉግዘምበርግ ያደረገውን የስራ ጉብኝት በተሳካ ሁኔታ አጠናቆ ተመለሰ

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሐራ መሐመድ የተመራውና ከ20 በላይ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችን ያቀፈው የንግድ ልኡካን ቡድን በቤልጅየም እና ሉግዘምበርግ ሲያደርግ የነበረውን የንግድ ለንግድ (B2B) ግንኙነት እና የስራ ጉብኝት በተሳካ ሁኔታ አከናውኖ ወደ ሀገሩ ተመልሷል፡፡

በብራሰልስ፣ ቤልጅየም በተካሄደው በዚህ ታሪካዊ የቢዝነስ ፎረም ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የአዲስ ቻምበር መሪዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ይህ የንግድ መድረክ በሁለቱ ወገኖች መካከል አዲስ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የንግድ ልኡካን ቡድንም በቆይታው ልምድና ተሞክሮን ለመቅሰም የሚያስችሉትን የተለያዩ የኢንቨስትመንት መሰረተ ልማቶችን እና ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝቷል፡፡

ይህን ታላቅ የኢትዮ-ቤልጅየም እና ሉግዘምበርግ የቢዝነስ ፎረም የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር)፡የቤልጅየም እና ሉግዘምበርግ የንግድ ምክር ቤት (CBL-ACP)፡ በብራሰልስ የሚገኘው የኢፌዲሪ ኤምባሲ፡የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የቤልጅየም ኤምባሲ በጋራ አዘጋጅተውታል፡፡

የቤልጅየም እና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትብብር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል። በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ መጠን ከ350 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውም በየዓመቱ የ12 በመቶ ፈጣን እድገት እያሳየ ይገኛል።

ቤልጅየም እንደ መድኃኒት ምርቶች (pharmaceuticals)፣ ማሽነሪዎች፣ ፕላስቲክ እና ኬሚካሎችን ወደ ኢትዮጵያ የምትልክ ሲሆን፤ በአንጻሩ ኢትዮጵያ እንደ ቡና እና የአበባ ምርቶች (floriculture) ያሉ የግብርና ውጤቶችን ወደ ቤልጅየም ትልካለች።

ይህ በጋራ የተዘጋጀው የንግድ ኮንፈረንስ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ እመርታ የታየበት መሆኑ ተገልጿል።

 

አዲስ ቻምበር የግሉ ዘርፍ አገልጋይ!

wpChatIcon
wpChatIcon