አዲስ ቻምበር ‘የንግዱ ማህበረሰብ ሚና ለሰላም ግንባታ’ በሚል የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ በስካይላይት ሆቴል አካሄደ፡፡

የንግዱ ማህበረሰብ የሚያነሳቸውን ጉዳዮች በአዲስ ቻምበር በኩል ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲቀርቡ ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ጥሪ አቅርበዋል፡ ፤

አዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የንግድና ኢንቨስትመንት ምህዳር እንዲሻሻልና አባላቱ የሚገጥማቸውን ተግዳሮቶች መፍትሄ እንዲያገኙ የማድረግ ሃላፊነቱን ከሚወጣባቸው መንገዶች መካከል አንዱ በተለያዩ ሀገራዊና የንግድ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ምክክር ማድረግ ነው ::

የዚሁ አንድ አካል የሆነው የምክክር መድረክ ‘የንግዱ ማህበረሰብ ሚና ለሰላም ግንባታ ’ በሚል ርእሰ ጉዳይ የተካሄደ ሲሆን ንግድና ሰላም ያላቸው ትስስር እና ለሰላም ግንባታ የግሉ ዘርፍ ያለው ሚና የሚሉ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይትና ምክክር ተደርጎባቸዋል ፡፡

በምክክር መድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት/ አዲስ ቻምበር/ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ እንዳሉት ለንግድና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ሰላምና መግባባት በጣም አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው በሁሉም ቦታ ሰላም እንዲረጋገጥ የንግዱ ህብረተሰብ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ማበርከቱን እንዲቀጥል አሳስበዋል፡ ፡

በሀገሪቱ ያሉ ሁሉም ያገባኛል የሚሉ ወገኖች ይልቁኑም የንግዱ ህብረተሰብ በሀላፊነት ስሜት በሰከነ መንገድ በየደረጃውና በያለበት ተቀራርቦ ለሰላም መስፈን ልዩ ሚና እንዲጫወት ጥሪ አስተላልፈዋል ፡፡

ንግድ ምክር ቤታቸውም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሰላማዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ለማስቀጠል የግሉ ዘርፍና የመንግስት ትብብር ሚና ከፍተኛ እንደሆነ በመገንዘብ ንግድ ለሰላም በሚል የተዘጋጀው የምክክር መድረክ በንግዱ ህብረተሰብ ዘንድ ሰፊ ግንዛቤን በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡ ፤

በመድረኩ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንደተናገሩት አንጋፋው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት እንዲህ አይነቱን ሀገራዊ እና ጠቃሚ የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱ እጅጉን የሚያስመሰግነው መሆኑን ጠቅሰው አዲስ ቻምበር የንግዱን ማህበረሰብ ጉዳዮች በተደራጀ ሁኔታ ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እንዲያቀርብ ጥሪ አቅርበዋል፡ ፤

በመድረኩ የቁልፍ መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ሕብረት ዋና ጸሐፊ ሊቀትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደተናገሩት ሰላም ለሰዎች ብቻ ሳይሆን ለፍጥረታት ሁሉ ከፈጣሪ የተሰጠ ጸጋ ነው ብለዋል፡፡

በሰላም እጦት ሳቢያ ዋነኛ ተጎጂው የንግዱ ህብረተሰብ እንደሆነ ጠቅሰው ዘላቂ ሰላምን በሀገራችን ለማረጋገጥ የሀይማኖት አባቶች፤የአገር ሽማግሌዎች ከንግዱ ሕ/ሰብ በትብብር መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ዋና ፀሃፊው ቀሲስ ታጋይ አክለውም የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በንግድና ሰላም ዙሪያ የሚሰራውን መልካም ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው ተቋማቸው ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር በዚህ ጉዳይ አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዋል ፡ ፡

በመድረኩ ላይ የመነሻና ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ‘ ሰላም በኮርፖሬት ንግድ እይታ’ በዶ/ር ጥላሁን በጅቷል ፤ ‘ሰላም፤ የህግ የበላይነትና ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ’ በአቶ ልኡል ሰገድ ግርማ እንዲሁም ‘የንግዱ ማህበረሰብ ሚና ለሰላም ግንባታ’ በመጋቢ ታምራት አበጋዝ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡ ፤

ውይይቱን ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ የመራው ሲሆን የአዲስ ቻምብር ዋና ፀሀፊ ዶ/ር መሰረት ሞላ በማጠቃለያ መልእክታቸው የምክክር መድረኩ በልዩ ልዩ የሰላም ነክ ጉዳዮች ላይ የንግዱ ህብረተሰብና መንግስት ተቀራርበው እንዲሰሩ ከማድረጉም በላይ ችግሮች ስር ሳይሰዱ ቶሎ የመቀረፍ እድሉን በማግኘት መፍትሄዎቹንም በጋራ ለማፈላለግ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡ ፡

በመድረኩ ላይ የተለያዩ ሀይማኖት አባቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎች፤የአዲስ ቻምበር የቦርድና የቀድሞ አመራሮች፤ የምክር ቤቱ የበጎ ፈቃድ አምባሳደሮች፤ታዋቂ ግለሰቦችና ነጋዴዎች፤ የመንግስት ሀላፊዎችና የአጋር ተቋማት ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡ ፤

አዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በቀጣይም የንግዱን ማህበረሰብ የተመለከቱ ትልልቅ የአድቮኬሲ ጉዳዮች በማንሳት ለምክክር የሚያቀርብ መሆኑ ተጠቁሟል፡ ፤

አዲስ ቻምበር ባላፈው ወርም ከአለም አቀፉ የግል ዘርፍ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር በታክስና ጉምሩክ አሰራሮች ዙሪያ የመንግስትና ግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱ ይታወቃል፡ ፤

wpChatIcon
wpChatIcon