የኑሮ ውድነት ፕሮጀክት

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ
መሰንበት ሸንቁጤ የግሉ ዘርፍ ጥምረት በኑሮ ውድነት ፕሮጀክት ትግበራን ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀ መርሀ ግብር ላይ ያደርጉት ንግግር
ሒልተን ሆቴል ፣
ሐምሌ 14፣2014
አዲስ አበባ
_ክቡር አቶ ጃንጥራ አባይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ
_ክቡር አቶ አደም ኑር የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሃላፊ
_ክቡራን የመንግስት ሀላፊዎች
_ክቡራን የም/ቤታችን የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት
_ውድ የንግድ ም/ቤታችን አባላት፤
_የተከበራችሁ የም/ቤታችን አጋር አካላት
_ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች፤
_ውድ የሚዲያ ባለሙያዎች
_ክቡራትና ክቡራን፤
ከሁሉ አስቀድሜ ጥሪያችንን አክብራችሁ የኩባንያ ማህበራዊ ኃላፊነትን
የምንወጣበት “የግሉ ዘርፍ ጥምረት በኑሮ ውድነት” የሚል የተቀደሰ ፕሮጀክትን
ይፋ በምናደርግበት መርሀግብር ላይ ስለተገኛችሁ ልባዊ ምሥጋናዬን በራሴ እና
በምክር ቤቱ ስም አቀርባለሁ፡፡
ክቡራትና ክቡራን
እንደሚታወቀው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት/ አዲስ
ቻምበር ላለፉት 75 ዓመታት የንግዱ ማኅበረሰብ እንደራሴ ሆኖ አገልግሎት
እየሰጠ ያለ አንጋፋ ተቋም ነው።
ምክር ቤቱ የግሉን ዘርፍ በማጠናከር በሀገሪቱ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ
የበኩሉን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡ በተለይም ለንግድ እና ኢንቨስትመንት
ምቹ ከባቢ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ፤ የንግዱን ሕብረተሰብ በአገሪቱ የኢኮኖሚያዊ
ዕድገት ድርሻውን ከፍ ለማድረግ እና ጠንካራ የቢዝነስ ዘርፍ እንዲፈጠር ዘርፈ
ብዙ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል።
ከንግድ ድጋፍ አገልግሎት በተጨማሪ ምክር ቤቱ ከአባላቱ ጋር በመሆን በበርካታ
የልማት ስራዎችና በተለያዩ ወቅቶች በዜጎችና በሀገር ላይ ችግር ሲገጥምም
ቀድሞ በመድረስ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
ክቡራትና ክቡራን
ማህበራዊ ሀላፊነትን ከመወጣት አንጻር በቅርቡ በኮቪድ ምክንያት ለተጎዱና
በጦርነት ሳቢያ ለተፈናቀሉ ዜጎቻችን ድጋፍ በማድረግ ወገናዊ አጋርነታችንን
አሳይተናል፡፡
የእናንተው ንግድ ምክር ቤት በቀጣይነትም በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን መልሶ
በማቋቋም ረገድ ከግሉ ዘርፍ ጋር በመሆን የአይነትና የቁሳቁስ ድጋፍን ጨምሮ
የተለያዩ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ
ይገኛል።
ክቡራትና ክቡራን
ም/ቤታችን በሀገሪቱ በተለይም በከተማችን እየሰፋ የመጣውን ድህነት፣ የኢኮኖሚ
ችግሮችና የዋጋ መናር በዜጎች፣ ነዋሪዎችና በተቀጣሪ ሠራተኞች ላይ
ያስከተለውን ከፍተኛ የኑሮ ውድነት በመገንዘብ አባላቱ ሊያደርጉ ስለሚገባው
ተጨባጭ የማህበራዊ ኃላፊነት ስራዎች የግንዛቤ ስራዎችን ይሰራል፡፡
ይህንን ተከትሎ በቅርቡም የምክር ቤታችን የቦርድ አመራር ለጽ/ቤቱ ባስቀመጠው
አቅጣጫ መሠረት የድጋፍ ሥራው ፕሮጀክት ጽንሰ-ሀሳብ እንዲቀረጽለት
ባስተላለፈው መመሪያ መሠረት ይህ ዛሬ የምንወያይበት ረቂቅ የፕሮጀክት ሃሳብ
እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡
ይህ ፕሮጀክት በከተማችን የተለያዩ አከባቢዎች ነዋሪ ለሆኑ ችግረኛ ቤተሰቦችና
ግለሰቦች በያዝነው የክረምት ወራት የምንደርስበት ፕሮጀክት ነው።
በተለይ ይህ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከእናንተው የንግዱ ማህበረሰብ
አባላት ጋር በመተባበር የምንሰራው የበጎ አድራጎትና የልማት ስራ፣ ማእድ
ማጋራት የአቅመ ደካማ ዜጎች መኖርያ ቤቶችን ማደስና የችግኝ ተከላ
ፕሮግራም የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ከእያንዳንዱ ስኬት ጀርባ እኛ የሚለው ሀሳብ አለና እኛ በጥምረትና በመተሳሰብ
በመስራት አዲስ ቻምበር የጀመረውን በጎ ተግባር እናንተው አባሎቻችን
እንደምትቀላቀሉን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ለዜጎች አለኝታ በመሆን የተሻለ ሀገርና ማህበረሰብ እንዲፈጠር የንግዱ ማህበረሰብ
ማኅበራዊና ሞራላዊ ግዴታውን ይወጣል ብለንም እናምናለን፡፡
ምክር ቤታችን ከአባላቱ ጋር የአረንጓዴ አሻራንም ለማሳረፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ
በተጀመረው መርሃግብር ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክት ይሆናል፡፡
ክቡራትና ክቡራን
በእርግጥ ኩባንያዎች በተናጠልና በያላችሁበት የምትወጡትን የማህበራዊ
ሀላፊነት ስራ እናደንቃለን፡፡ እውቅናም እንሰጣለን ይሁን እንጂ
ሁኔታ አቅም ፈጥረን ብንሰራ ደግሞ ተጽእኖ እንፈጥራለን ፡፡
በተደራጀ
ይህ እዚህ የተሰባሰበው አቅም በራሱ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ የልማት አጋር
ነው ብለን እናምናለን፡፡
በስተመጨረሻም ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በተለይም በምግብ ማምረት፣
ከውጪ ማስገባትና ማከፋፈል፣ በሆቴልና ሬስቶራንት፣በኮንስትራክሽን፣ በአረንጓዴ
ኢኮኖሚ፣በፋይናንስ፣በጅምላና ችርቻሮ፣ በትራንስፖርት ማቅረብ፣ በበጎ ፈቃድ
እና በመሳሰሉት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዲሁም የከተማ
አስተዳደሩ ከምክር ቤታችን ጋር በመሆን ለዚህ ለተቀደሰ አላማ አብረው እንዲሰሩ
በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
አመሰግናለሁ