የሚኒስትሮች ምክር ቤት የግብርና ዘርፍን ከተለምዶአዊ አሰራር ወደ ቢዝነስ መር ስርአት ለማሸጋገር ያግዛል ያለውን “የግብርና ቢዝነስ ኩባኒያ አዋጅ” ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱ ይታወቃል።
ይህ አዋጅ ኋላ ቀር የግብርና አሠራር ተወስነው የቆዩ አነስተኛ አርሶ አደሮችን፣ አርብቶ አደሮችንና ከፊል አርብቶ አደሮችን ወደ ዘመናዊና ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓት ለማሸጋገር ያለመ ነው።
የዚህ ሪቂቅ አዋጅ ዋነኛ ትኩረት አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አምራቾች በ “ክላስተር” በማደራጀት ወደ ግብርና ቢዝነስ ኩባኒያነት መለወጥ ነው።
አዲሱ ሕግ አርሶ አደሩ ያለውን መሬት የመጠቀም መብት፣ የእንስሳት ሀብትና ጉልበት ወደ ካፒታል በመለወጥ የኩባኒያ ባለቤትና ባለድርሻ እንዲሆን ዕድል ይከፍታል።
ይህም አርሶ አደሩ በግል ከመልፋት ይልቅ በጋራ በመደራጀት በገበያ ላይ የመደራደር አቅሙን እንዲያሳድግ፣ ምርቱን እንዲያሰባስብና እሴት በመጨመር የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ እንደሚያስችለው አዋጁ ያስረዳል።
በአዋጁ መሠረት አንድ የግብርና ቢዝነስ ኩባኒያን ለመመስረት ዝቅተኛ የአባላት ቁጥር ተቀምጧል።
በአዝርዕት ዘርፍ የተሰማሩ ከሆኑ ቢያንስ 300 አባላት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ወይም በእንስሳት እርባታ ዘርፍ ከሆነ ደግሞ ቢያንስ 150 አባላት ሊኖሩት ይገባል።
ኩባኒያዎቹ ሲመሰረቱ ዝቅተኛ የተከፈለ ዋና ካፒታላቸው ከ1.5 ሚሊዮን ብር ማነስ የለበትም።
እያንዳንዱ አባል በኩባኒያው ውስጥ ሊኖረው የሚችለው የአንድ ድርሻ (Share) ዋጋም ከ1,000 ብር በታች እንዳይሆን ተደንግጓል።
የግብርና ቢዝነስ ኩባኒያዎቹ እንደ ማንኛውም ዘመናዊ የንግድ ተቋም በጠቅላላ ጉባኤ፣ በሥራ አመራር ቦርድ እና በዋና ሥራ አስኪያጅ የሚመሩ ይሆናሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ኩባኒያዎቹ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችን የሚጠቁሙና ሙያዊ ምክር የሚሰጡ፣ “የአማካሪ ቦርድ” እንዲኖራቸው አዋጁ ይፈቅዳል፣ የአማካሪ ቦርድ የስራ አባላት ዘመንም ሦስት አመት ነው።
ይህም የኩባኒያዎቹ አመራር በሳይንሳዊና በዘመናዊ የቢዝነስ ዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማድረግ ነው።
ይህንን ሽግግር ለማገዝም ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችን ረቂቅ አዋጁ አካቷል።
የግብርና ቢዝነስ ኩባኒያዎቹ ለሥራቸው የሚያስፈልጉ የግብርና ግብዓቶችና ቴክኖሎጂዎችን፣ የእርሻ መሣሪያዎችንና ተሽከርካሪዎችን እንዲሁም መለዋወጫዎችን ከውጭ ሲያስገቡ “ከታክስ ነፃ” የመሆን መብት ይኖራቸዋል።
የግብርና ቢዝነስ ኩባኒያ አባላት ያመረቱተትን የግብርና ምርት ሲሽጡ ወይም ከኩባኒያው በሚያገኙት የትርፍ ክፍፍል ላይ የገቢ ግብር አይከፍሉም፡፡
ሆኖም ኩባንያው ከሚያገኘው ገቢ ላይ በገቢ ግብር አዋጁ መሰረት ግብር ይከፍላል፡፡
በተጨማሪም ኩባንያዎቹ ግብዓቶችን ለማስገባት ለሚያስፈልጋቸው የውጭ ምንዛሬ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ለሥራ አመራር ቦርድና ለአባላት የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እንደሚመቻቹ እንደሚደረግ ረቂቅ መመሪያው ያሳያል።
ግንቦት 18 በተካሄደው 55ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ፣ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል።
