የኢትዮ-ዱባይ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሄደ

የኢትዮ-ዱባይ የንግድ ፎረም በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል ዛሬ ተካሂዷል።

መድረኩ በአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር)፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት ኤምባሲዎችና በዱባይ ቻምበር የጋራ ትብብር የተዘጋጀ ነው።

በፎረሙ ላይ በታዳሽ ኃይል፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ አይቲ፣ ሕክምና፣ ምግብና መኪና መገጣጠም ዘርፎች የተሰማሩ የዱባይ ኩባንያዎች ተሳትፈው ምርትና አገልግሎታቸውን ያስተዋወቁ ሲሆን፣ ከሀገር ውስጥ ተቋማት ጋር የቢዝነስ ትስስርና የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።

በዚሁ መድረክ ላይ ወደ 400 የሚጠጉ የአዲስ ቻምበር አባል ኩባንያዎች ተገኝተዋል።

የአዲስ ቻምበር ምክትል ፕሬዝዳንት ኢንጂነር አበበ ጉርሜሳ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፣ የዱባይ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ አዲስ ቻምበር ከዱባይ ቻምበር ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ሁለቱ ምክር ቤቶች እ.ኤ.አ. በ2024 ንግድና ኢንቨስትመንትን በጋራ ለማስፋፋት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ መጠን እ.ኤ.አ. በ2025 ከ6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል።

ላለፉት 79 ዓመታት የንግዱን ማህበረሰብ ሲያገለግል የቆየው አዲስ ቻምበር፣ ይህ መድረክ የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጿል።

wpChatIcon
wpChatIcon