የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት/ አዲስ ቻምበር/ ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድን ፕሬዝዳንት አድርጎ መረጠ ፡፡

አዲስ ቻምበር ጥር 8 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው 18ተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድን ፕሬዚዳንት፤ ኢንጂነር አበበ ጉርሜሳን ምክትል ፕሬዚዳንት እና ሌሎች ዘጠኝ የቦርድ አባላትን በመምረጥ ተጠናቋል፡ ፡

በዕለቱ ጉባኤው የመረጣቸውና ያፀደቃቸው የቦርድ አባላት ወ/ሮ ሳራ ሰለሞን፤ አቶ አዲሱ ጌታሁን፤ ወ/ሮ ዘሀራ አህመድ፤ አቶ መስፍን ጋረድ፤ አቶ ዳምጤ ዳኘው፤ አቶ ሀብታሙ ሀይሉ፤አቶ አይችሉህም ከበደ ፣አቶ ተሰፋዬ ገ/ኪዳን እና ወ/ሮ ግሩምነሽ ይመር ናቸው፡ ፡

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ቡዜና አልቃድር እንደተናገሩት አዲስ አበባ ለንግድ ሥራና፣ ለሥራ ፈጠራ እንዲሁም ለኢኮኖሚ ልማት እድገት አመቺነቷ የተረጋገጠ የኢንቨስትመንት ማዕከል እንድትሆን ንግድ ምክር ቤቱ የበኩሉን ሚና አጎልብቶ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀው እንደ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ያሉ አደረጃጀቶች ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል፡ ፡

በጉባኤው ላይ ተገኝተው መልእክታቸውን ያስተላለፉት የከተማዋ ንግድ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው ንግድ ምክር ቤቱ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ መካከል አገናኝ ድልድይ ሆኖ የሚጫወተውን ሚና የበለጠ ማጠናከር እንዳለበት አሳስበው አዲሶቹ አመራሮች ነጋዴውን በስፋት በማሳተፍ የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡ ፡

በምክር ቤቱ የተጀመረውም ሪፎርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልፀው በየደረጃው ያሉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትን ሊጠቅም የሚችል አገልግሎት ሰጪ ተቋም እንዲሆን መስራት እንዳለበት ተናግረዋል፡ ፡

አዲስ ቻምበር በካሄደው 18ተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የ2016 ዓ.ም አፈፃፀም ሪፖርት፣ የ2016 የውጭ ኦዲት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበት ፅድቋል ፡፡

አዲሷ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ በ 355 ድምጽ ለቀጣዮቹ 2 አመታት በፕሬዚዳንትነት የሚያገለግሉ ይሆናል፡ ፡

ለፕሬዚዳንትነት በተፎካካሪነት ከተወዳደሩት መካከል ወ/ሮ ሳራ ሰለሞን መሆናቸው ለማወቅ ተችሏል፡ ፡