የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ( ዶ/ር) ከአዲስ ቻምበር የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትና ከምክር ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሄዱ፡፡
በሀገር ውስጥ የሚገኙ ንግድ ምክር ቤቶች አሁን አለም በሚጠይቀው ልክ እና ጥራት መጠን በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ ሚናቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ ሚኒስትሩ ከአዲስ ቻምበር የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
እንዲህ አይነት ተቋማት በሌሎች ሀገራት ለንግድና ኢኮኖሚ መዳበር ያላቸው ሚና ወሳኝ እንደሆነ የተናገሩት ሲሆን የሌሎች ሀገራትን ልምድ መውሰድ እንደሚገባ ምክረሃሳብ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ እንደ አዲስ ቻምበር የመሳሰሉ ንግድ ምክር ቤቶች የአለም አቀፍ የንግድ ትስስር መድረኮች ላይ እያበረከቱ ያሉትን አስተዋጽኦ በስፋት እንዲቀጥሉበት አሳስበዋል፡ ፡
ከዚህም ባለፈ ሚኒስትሩ ንግድ ምክር ቤቶች በሀገር ውስጥ ጠንካራ የንግድ ፖሊሲዎች እንዲወጡና እንዲተገበሩ የፖሊሲ አድቮኬሲ ስራዎችን በስፋት መስራትና የሚወጡ ንግድ ነክ ህጎችን ለንግዱ ማህበረሰብ የማስተዋወቅ ስራቸውን አጠናክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከአዲስ ቻምበር ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ አብሮ ለመስራት ጥብቅ ፍላጎት እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡
በተመሳሳይ የአዲስ ቻምበር ፕሬዚደንት የሆኑት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ በበኩላቸው የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ( ዶ/ር) ለንግድ ማህበረሰቡ ተወካዮች ጊዜያቸውን በመስጠታቸው ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ንግድ ምክር ቤታቸው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ አብሮ ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆነ ገልጸዋል ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ፕረዚደንቷ መንግስት ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አሳስበው ህጋዊ የንግድ ስርአት እንዲሰፍን ሚኒስቴር መስሪያቤቱና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ ጤናማ የንግድ ስርአት እውን እንዲሆን እንደ ገቢዎች መስሪያ ቤት ከመሳሰሉ የመንግስት ተቋማት ጋር ንግግር እያደረገ መሆንኑ አክለው ጠቅሰዋል፡፡
የንግዱ ማህበረሰብ በአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና እና በአለም የንግድ ድርጅት አባልነት እና እድሎች ዙሪያ ከወዲሁ እንዲዘጋጅ ንግድ ምክር ቤቱ አበክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡ ፡
በመጨረሻም የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አመራሮች በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ቅጥር ግቢ የሚገኘውን የወጪ ንግድ ማሳያ ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡