(አዲስ ቻምበር፤ ሀምሌ 11 ቀን 2018 አ.ም) በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አስተባባሪነት የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች የተሳተፉበት የ2018 በጀት ዓመት “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከተማ ሳሊተ ምህረት አከባቢ ተከናውኗል።
በዚህ መርኀ ግብር የአዲስ ቻምበር አመራሮች፤ የቦርድ አባላት፤ የኢትዮጵያ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች እንዲሁም የንግድ ምክር ቤቶች ተካፋይ ሆነዋል።
የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙን ያስጀመሩት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የንግዱ ማህበረሰብ አረንጓዴ አሻራን በማሳረፍ ለትዉልድ የምትምች ሀገር እንዲፈጥር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያ በየዓመቱ በምታካሂደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እስካሁን ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ትልቅ አገራዊ ሥራ መሰራቱን ገልጸው ይህ ስኬት ኢትዮጵያ የCOP32 አዘጋጅ ዝግጅት ሆና እንድትመረጥ እንዲሁም በተፈጥሮ እንክብካቤ ረገድ በዓለም ቀዳሚ ከሚባሉት ተርታ እንድትሰለፍ ማስቻሉን አብራርተዋል።
አዲስ ቻምበር ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣትን ጨምሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር ከተጀመረ አንስቶ የተስተካከለ እና ዘላቂነት ያለው ሥነ ምኅዳር ለመፍጠር ፣ የደን ሽፋንን ለማሳደግ፣ የግብርና ምርታማነትን ለመጨመር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
አዲስ ቻምበር የግሉ ዘርፍ አገልጋይ!
