ከ40 በላይ የንግድ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የኢትዮ-ዱባይ የንግድ ፎረም በዱባይ ሊካሄድ ነው።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) ከዱባይ ንግድ ምክር ቤትና ከኢትዮጵያ ኤምባሲ በተባበሩት አረብ ኤሚሬት ጋር በመተባበር በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች የተሰማሩ ከ40 በላይ የአዲስ ቻምበር አባል ኩባንያዎችና ባለሐብቶች የሚሳተፉበት ታላቅ የቢዝነስ ውይይትና ኮንፈረንስ በቀጣዩ መስከረም ወር መግቢያ በዱባይ ይካሄዳል ።

አንጋፋው አዲስ ቻምበር እ.ኤ.አ. መስከረም 2 ቀን 2026 በዱባይ በሚካሄደው የቢዝነስ ለቢዝነስ ውይይትና ፎረም ላይ፣ የሐገራችን አምራቾች፣ አገልግሎት ሠጪዎች ላኪዎችና አስመጪዎች እንዲሳተፉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሠራ ነው።

የዱባይ ባለሀብቶች እና ኩባንያዎች ከኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎች ጋር ፊት ለፊት በመገናኘት የንግድ፣የኢንቨስትመንትና የገበያ ትስስር ይፈጥራሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

አዲስ ቻምበርም በአምራች ኢንዱስትሪ ፣ በግብርና ፣ በላኪነት እና አስመጪነት ዘርፍ የተሠማሩ ኩባንያዎች በፍጥነት በአዲስ ቻምበር እንዲመዘገቡና ይህን የቢዝነስ ትስስር መድረክ እንዲጠቀሙበት ጥሪውን አቅርቧል ።

አዲስ ቻምበርና የዱባይ ቻምበር ንግድና ኢንቨስትመንት በማስፋፋት ረገድ በቅርቡ የጋራ መግባቢያ ሠነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።

የዚሁ አንድ አካል የሆነውና በባለፈው ግንቦት ወር በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል የተካሄደው የኢትዮ ዱባይ የቢዝነስ ኮንፈረንስ አንዱ ማሳያ ሲሆን ከ20 በላይ የዱባይ ባለሐብቶች በተገኙበት ከ300 በላይ የአዲስ ቻምበር አባል ኩባንያዎች የንግድ ለንግድ ውይይት መደረጉ ይታወቃል ።

አዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) ባለው አለም አቀፋዊ ስምና ከሌሎች ሐገራት ከተሞች ንግድ ምክርቤቶች ጋር ባለው የጋራ መግባቢያ ስምምነት መሠረት ለንግዱ ህብረተሰብ የገበያና የንግድ ትስስር በመፍጠር ኩባንያዎች ተወዳዳሪነታቸው እንዲጎለብት በመስራት ላይ ይገኛል።

የውጪ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እና በአዲስ አበባ በቢዝነስና በኢንቨስትመንት ዘርፍ በይበልጥ እንዲሳቡና እንዲሠማሩ ጥረት እያደረገ ነዉ።

 

በቅርቡ ከሚካሄደው የኢትዮ ዱባይ የቢዝነስ ፎረም በተጨማሪ በሌሎች ሐገራት ከተሞች የሚከናወኑ በርካታ የንግድ እና የገበያ ትስስር መድረኮችን ለንግዱ ማህበረሰብ እየተመቻቸ መሆኑም ለማወቅ ተችሏል ።

ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የቅርብ ጊዜ (የ2025) የንግድ ልውውጥ መጠናቸው ከ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ ።

ባለፉት 79 ዓመታት የንግዱን ማህበረሰብ እያገለገለ የሚገኘው አንጋፋው አዲስ ቻምበር የሁለቱ ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር እንዲያድግ ካደረጉ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑ ተመላክቷል።

https://forms.gle/gCGAenqEzCx4nqxEA

#አዲስ ቻምበር፣ የንግዱ ማህበረሰብ ድምፅ እና አገልጋይ