በአዲስ አበባ በሚካሄደው 32ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አዲስ ቻምበር የግሉን ዘርፍ ጉዳይ እንደሚያደራጅ ተገለጸ፡፡
በየዓመቱ የዓለም ሀገራት መሪዎች፣ የአየር ንብረት ባለሙያዎች እና ተደራዳሪዎች ተሰብስበው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስ እና ለተከሰቱ ጉዳቶች የሚደረግ ድጋፍን ለመወሰን በሚመክሩበት ትልቁ ዓለም አቀፍ COP32 መድረክ ላይ የግሉን ዘርፍ ጉዳዮች አዲስ ቻምበር የማስተባበር ሚና ለመጫወት እንዳቀደ ተገልጿል ፡፡
ኢትዮጵያ በኖቬምበር 2027 የምታስተናግደውን 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ለንግዱ ማህበረሰብ አለም አቀፍ የንግድና የኢንቨስትመንት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ትስስር መፍጠር የሚያስችል በመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ በንቃት ሊሳተፍበት የሚገባ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
አዲስ ቻምበር ከኔዘርላንዱ የልማት ድርጅት SNV እና GIZ ጋር በመተባበር የመጀመርያውን የአረንጓዴ ኢንቨስትመንት ፎረም እና ኤግዚቢሽን በእስካይላይት ሆቴል አካሂዷል፡፡
በፎረሙ አቶ ጳውሎስ ኩሳ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኃላፊ፡ የአዲስ ቻምበር የቦርድ አባላት እና ዋና ጸሃፊ የሚመለከታቸው የመንግስት እና አጋር ድርጅቶች ባለድርሻዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች እና ነጋዴዎች ተገኝተዋል፡፡
በርካታ ባለድርሻዎችን ባሳተፈው ፎረም እና ኤግዚቢሽን በአረንጓዴ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ አምራቾች ፡በመልሶ ጥቅም ማዋል ዘርፍ የተሰማሩ፡እንዲሁም በአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ፈጠራ እና አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች እና ባንኮች ምርት እና አገልግሎታቸውን ለእይታ አቅርበዋል፡፡
አረንጓዴ ኢንቨስትመንት የአካባቢ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚ እድገት የሥራ ፈጠራ እና ተወዳዳሪነት አስፈላጊ መሆኑን በንግግራቸው ያነሱት የአዲስ ቻምበር ዋና ጸሃፊ አቶ ዘካርያስ አሰፋ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም ከግሉ ዘርፍ የነቃ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ አንስተዋል፡፡
ይህንንም ውጤታማ ለማድረግ አዲስ ቻምበር ከጂአይዜድ (GIZ) ጋር በጋራ በመስራት የንግድ ማህበረሰቡን ለማገልገል እና ኢንተርፕራይዞችን በሽግግር ወቅት አስፈላጊ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያግዝ የአረንጓዴ ልማት ማዕከል በማቋቋም አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ቢሮ ትኩረት ከሚያደርግባቸው መካከል ንጹህ የሃይል አቅርቦት እና ፈጠራ፡ዘመናዊ የሃብት አጠቃቀም እና ቅልጥፍና እንዲሁም በትብብር መስራት እና የአረንጓዴ ፋይናንስ መሆናቸውን ያነሱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጳውሎስ ኩሳ የተቋማቸው ህልም የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት እና ማሳካት ብቻ ሳይሆን ዘላቂ አካታች እና ቀጣይነት ያለው እድገት ማምጣት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በስካይላይት ሆቴል በተካሄደው ፎረም አረንጓዴ ኢንቨስትመንት አሁናዊ ገጽታ ፡ያሉ ተግዳሮቶች እንዲሁም በቀጣይ ሊሰሩ የታሰቡ ስራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ምንስቴር፡ በብሄራዊ ባንክ፡በቦሌለሚ ኢንደስትሪያል ፓርክ እና ግሎባል ግሪን ግሮዎዝ ኢኒስቲቲውት የተደረገ ሲሆን ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ተነስተው ማብራያ ተሰቶባቸዋል፡፡
አዲስ ቻምበር የግሉ ዘርፍ ድምጽ
