አዲስ ቻምበር 6ኛውን ዓለም አቀፍ የማኑፋክቸሪንግ፣ ቴክኖሎጂ እና የኮስሞቲክስ ኤክስፖ (MATEX-ETHIOPIA 2026) በመጪው ህዳር 24 እስከ 26 ቀን 2019 ዓ.ም. በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በደመቀ ሁኔታ እንደሚያካሂድ ምክር ቤቱ በዛሬው እለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቋል።

አዲስ ቻምበር ነሃሴ 5 ቀን 2018 አ.ም፡- ይህን ያስታወቀው ምክር ቤቱ በዛሬው እለት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡ ምክር ቤቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ንግድ ትርኢቶችን በአገር ውስጥ በማካሄድ ፈር ቀዳጅ መሆኑን እና ዛሬ ላይ መሰል መድረኮች እንዲስፋፉ በማድረግ፤ ትላልቅ የንግድ ትርኢት ቦታዎችን በባለቤትነት በመያዝ እና በማስተዳደር ምክር ቤቱ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተብራርቷል፡፡

“Unlocking the AfCFTA Market: Catalyzing Manufacturing & Intra African Trade through MATEX-ETHIOPIA 2026” በሚል ታላቅ መሪ ቃል በመጪው ህዳር ወር የሚካሄደው አዲስ ቻምበር 6ኛው ዓለም አቀፍ የማኑፋክቸሪንግ፣ ቴክኖሎጂ እና የኮስሞቲክስ ኤክስፖ (MATEX-ETHIOPIA 2026) የቢዝነስ ለቢዝነስ ውይይቶች፤ የቢዝነስ ጉባኤ፤ የሽልማት ፕሮግራም፤ የቢዝነስ አጋርነት ስምምነቶች የሚደረጉበትና በርካታ የንግድ ተቋማትና ጎብኚዎች የሚሳተፉበት እንደሚደረጉበት የገለጹት የምክር ቤቱ ም/ዋና/ጸሃፊ አቶ ካሳሁን ማሞ ናቸው፡፡

በዚህ የንግድ ትርኢት ላይ ከተለያዩ የአለማችን አገራት ለአብትም ከአፍሪቃ ፤ ከመካከለኛው ምስራቅ፤ ከአውሮጳና ከኢሲያ የተውጣጡ አምራቾች፤ የምግብ ማቀነባበርና አግሮ ኢንዱስትሪዎች፤የጨርቃጨርቅና ጋርመንት፤የፋሽን ምርት፤ የቆዳ ውጤት አምራቾች ፤የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ፤ የእንጨት ውጤቶችና ምርቶች፤ የፕላስቲክና ማሸጊያ አምራቾች፤ የግንባታ እቃ አቅራቢዎችና አምራቾች፤ የመረጃ ቴክኖሎጂ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ም/ዋና ጸሃፊው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አክለው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ ቻምበር 6ኛው ዓለም አቀፍ የማኑፋክቸሪንግ፣ ቴክኖሎጂ እና የኮስሞቲክስ ኤክስፖ (MATEX-ETHIOPIA 2026) በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተከሰቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች በማስተዋወቅ እንዲሁም ጠንካራ የቢዝነስ ትስስር የሚፈጠርበት መድረክ እንደሆነ የገለጹት የምክር ቤቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን መምሪያ ተ/ስራ አስኪያጅ አቶ መብራቱ በላቸው ናቸው፡፡

ከ150 በላይ የውጭ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት 6ኛው ዓለም አቀፍ የማኑፋክቸሪንግ፣ ቴክኖሎጂ እና የኮስሞቲክስ ኤክስፖ (MATEX-ETHIOPIA 2026) ለአገር ውስጥ ስራ ፈጣሪዎች መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር ለማወቅ ተችላል፡፡

አዲስ ቻምበር የግሉ ዘርፍ አገልጋይ!