ዳሸን ባንክ በገነባው ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ለማጋራት እየሰራ ነው::

የአዲስ ቻምበር አይ ቲ እና ኮሙኒኬሽን ክፍል ሰራተኞች ማዕከሉን ጎብኝተዋል፡፡
ዳሸን ባንክ ዘመናዊና በግል የፋይናንስ ተቋም ደረጃ የመጀመሪያ የሆነውን ቲር 3 (Tier III) የመረጃ ማዕከል የገነባው በ230 ሚሊዮን ብር ወጪ ነው ፡፡
የባንኩ ቺፍ ኢንፎርሜሽን መኮንን አቶ ሽመልስ ለገሰ ለአዲስ ቻምበር እንዳሉት መረጃ ማዕከሉ ከዳሸን ባንክ ባሻገር ለሌሎች ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት ይሰጣል ፡፡
በተለይም የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች ሰርቨሮቻቸውን አምጥተው በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስቀምጡበትና የሚጠቀሙበት የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት (ቦታ) መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
የመረጃ ማዕከሉ ከፍተኛ ኃይል ያላቸውን ከ1,000 ያላነሱ ሰርቨሮችና ሌሎች ተያያዥ የኔትወርክ መሳሪያዎችን የማስተናገድ አቅም አለው፡፡
በጥገና ወቅትም መደበኛ የባንኩን ስራ ሳያቋርጥ አመቱን ሙሉ አገልግሎት መስጠት ይችላል ብለዋል፡፡
የመረጃ ማዕከል ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትን ከየትኛውም ቦታ ማግኘት የሚያስችልና ባንኩ የተለያዩ አዳዲስ አገልግሎቶችን ያለምንም ችግር ወደ ስራ ለማስገባት ያግዛል፡፡
የማዕከሉ ግንባታ በኢንዱስትሪው በተለይም የውጭ ባንኮች ሲገቡ የሀገር ውስጥ ባንኮችን የተወዳዳሪነት አቅም በማሳደግ የጎላ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡
ዘመናዊው የመረጃ ማዕከሉ በውስጡ የዳታ ሴንተር የኔትዎርክ ኦፕሬሽን ፣ የደህንነት ኦፕሬሽን፣ የሶፍትዌር ዲፋይኒንግ ሴንተር እና ማንኛውንም እንስቃሴ የሚቆጣጠር CCTV ካሜራዎች ተገጥመውለታል፡፡