በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሠማሩ የአረብ ኤሜሬት ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የአዲስ-ሻርጃህ የንግድ ፎረም በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) ከኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከሻርጃህ ንግድ ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ኤምባሲና ከኢትዮጵያ ኤምባሲ በተባበሩት አረብ ኤሚሬት ጋር በመተባበር በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች የተሰማሩ የሻርጃህ ከተማ ኩባንያዎችና ባለሐብቶች የሚሳተፉበት ታላቅ የቢዝነስ ውይይትና ኮንፈረንስ በተያዘው ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል ።

በአዲስ አበባ በሚካሄደው የቢዝነስ ለቢዝነስ ውይይትና ፎረም ላይ፣ የሐገራችን አምራቾች፣ አገልግሎት ሠጪዎች ላኪዎችና አስመጪዎች ይሳተፋሉ ።

የሻርጃህ ባለሀብቶች እና ኩባንያዎች ከአዲስ ቻምበር አባል ኩባንያዎች እና ከኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎች ጋር ፊት ለፊት በመገናኘት የንግድ፣የኢንቨስትመንትና የገበያ ትስስር ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

አዲስ ቻምበርም በአምራች ኢንዱስትሪ ፣ በግብርና ፣ በአገልግሎት፣በላኪነት እና አስመጪነት ዘርፍ የተሠማሩ ኩባንያዎች እንዲሳተፉና ውጤታማ የቢዝነስ ትስስር እንዲፈጥሩ ቅድመ ዝግጅት እንዳጠናቀቀ ለማወቅ ተችሏል ።

በዚህ ታላቅ የንግድ መድረክ ላይ አዲስ ቻምበርና የሻርጃህ ቻምበር ንግድና ኢንቨስትመንት በማስፋፋት ረገድ የጋራ መግባቢያ ሠነድ በፕሬዚዳንቶቻቸው በኩል ይፈራረማሉ ።

አዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) ባለው አለም አቀፋዊ ስምና ከሌሎች ሐገራት ከተሞች ንግድ ምክርቤቶች ጋር ባለው የጋራ መግባቢያ ስምምነት መሠረት ለንግዱ ህብረተሰብ የገበያና የንግድ ትስስር በመፍጠር ኩባንያዎች ተወዳዳሪነታቸው እንዲጎለብት አበክሮ በመስራት ላይ ይገኛል።

ንግድ ምክር ቤቱ የውጪ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለይ በአዲስ አበባ በቢዝነስና በኢንቨስትመንት ዘርፍ በይበልጥ እንዲሳቡና እንዲሠማሩ ጥረት እያደረገ ይገኛል ።

በዚህ ሳምንት ከሚካሄደው የአዲስ-ሻርጃህ የቢዝነስ ፎረም በተጨማሪ በሌሎች ሐገራት ከተሞች የሚከናወኑ በርካታ የንግድ እና የገበያ ትስስር መድረኮችን ለንግዱ ማህበረሰብ እየተመቻቸ መሆኑም ለማወቅ ተችሏል ።

ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የቅርብ ጊዜ (የ2025) የንግድ ልውውጥ መጠናቸው ከ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ ።

ባለፉት 80 ዓመታት የንግዱን ማህበረሰብ እያገለገለ የሚገኘው አንጋፋው አዲስ ቻምበር የሁለቱ ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር እንዲያድግ ካደረጉ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑ ተመላክቷል።

#አዲስ ቻምበር፣ ከ1939 ዓም ጀምሮ የንግዱ ማህበረሰብ ድምፅ እና አገልጋይ