የሚዲያ ባለሙያዎች እና ተቋማት ለቢዝነስ ዘገባዎች ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ

በይድነቃቸው ዓለማየሁ
አዲስ ቻምበር በርካታ ንግድ ነክ የሆኑ የመረጃ ፍሰት ፤እንዲሁም የጥናትና ምርምር ውጤቶች ክምችት ያለው ተቋም ነው፡፡
ነገር ግን ለንግዱ ሕብረተሰብ እና ለፖሊሲ አዉጪዎቸ ጠቃሚ የሆኑ እኒህ መረጃዎች ተደራሽ እንዲሆኑ የሚዲያ ባለሙያዎች ሽፋን መስጠት አለባቸው ።
አዲስ ቻምበር ባዘጋጀው የሚዲያ ባለሙያዎች እና ባለድርሻዎች የምክክር መድረክ ላይ የንግድ ም/ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም አብዛኛውን የአገራችንን ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሰው የግል ዘርፍ የቢዝነስና የኢኮኖሚ ጋዜጠኞች ትኩረት ሰጥተው መዘገብ አለባቸው ብለዋል ።
ለዚህም ንግድ ም/ቤቱ ከበርካታ የሚዲያ ተቋማት ጋር ያለውን ትስሰር አጠናክሮ ይቀጥላል።
የንግዱ ሕ/ሰብ ጥያቄዎች ፤የንግድ ነክ ፖሊሲ ጉዳዮች ይበልጥ ትኩረት እንዲያገኙ እና ተደራሽ እንዲሆኑ ንግድ ም/ቤቱ የራሱን ሬዲዮ ጣቢያ ለመክፈት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል ።
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ተወካይ አቶ ካሣሁን መንግሥቴ በበኩላቸው የመገናኛ ብዙሃን በንግድ ሥራ ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን በማረም ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት እንዲጎለብት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በተጨማሪም የንግድ ድርጅቶችን ተጠቃሚ እና ምርታማነት በሚያሳድጉ ሥራዎቹ ላይ የሚዲያ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል ።
ለአንድ ቀን በሚቆየው መድረክ ላይ ከፍተኛ የሚዲያና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች በቢዝነስ መረጃ አሰባሰብ እና አዘጋገብ፣ በሙያዊ ሥነምግባር ፤ በግልና የመንግሥት ትብብር ማጠናከር ላይ ያተኮሩ ገለጻ አድርገዋል ።
አንጋፋ ባለሙያዎች በትምህርት እና በሥራ ላይ የገኙትን ዕውቀትና ልምዳቸውን ያካፈሉ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል ።