የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በ2016 የሚያከናውናቸውን ንግድ እና ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት የሚያግዙ የንግድ ትርኢት መርሃ ግብሮችን አስተዋውቋል፡፡
በእለቱ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፡አምባሳደሮች፡ነጋዴዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻዎች ተገኝተዋል፡፡
ምክር ቤቱ በ2016ዓ.ም ሶስት አለም አቀፍ ንግድ ትርኢቶችን በአዲስ አበባ ኢግዚቢሽን ማእከል እና በሚሊኒየም አዳራሽ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል፡፡
የዓመቱ የንግድ ትርኢት መርሃ ግብር በተዋወቀበት ዝግጅት ላይ መልክት ያስተላለፉት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ምክር ቤቱ በሚያዘጋጃቸው ንግድ ትርኢቶች ላይ የሌሎች ሃገሮች ተሳታፊዎችን በመጋበዝ ሃገራችን ያላትን አቅም ተጠቅመን ከሌሎች ሃገሮች ነጋዴዎች ጋር የንግድ ልውውጥ ለማምጣት እንዲቻል እና የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ሌሎች እንዴት እንደሚሰሩ ማወቅ እንዲችሉ ለማገዝ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በወጭ እና ገቢ ንግድ የሃገር ውስጥ አምራቾች ምርቶቻቸውን ወደ ሌላ ሃገር ለመላክ ፡ማን እንደሚቀበላቸው ካለማወቅ እንዲሁም ተገቢውን የተግባቦት መንገድ ባለመከተል እና በሌሎች ክፍተቶች የተነሳ ችግር እንደሚገጥማቸው ያነሱት ፕሬዝዳንቷ መሰል የንግድ ትርኢቶች መዘጋጀታቸው የሃገር ውስጥ አምራቾች የውጭ ሃገር ነጋዴዎችን በቅርበት በማግኘት ችግሮቻውን ለመፍታት ያግዛቸዋል ብለዋል፡፡
የምክር ቤቱ ዋና ጸሃፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በበኩላቸው የተለያዩ ዘርፎች ላይ በማተኮር በምክር ቤቱ የሚዘጋጁት ንግድ ትርኢቶች የሃገራችንን መልካም ገጽታ ለማብሰር እንዲሁም እይታዎችን ወደ ንግድ እና ኢንቨስትመንት አቅጣጫ ለማዞር እንደሚያግዝ ገልጸው፡በዘንድሮ የንግድ ትርኢት በእርግጠኝነት ከ100 በላይ የውጭ ኩባንያዎች የሚሳተፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ምክር ቤቱም ከውጭ ሃገራት የንግድ ማህበራት ጋር በፈጠረው ግንኙነትም የቱርክ እንዲሁም የቻይና ኩባንያዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡
በንግድ ትርኢቶቹ ቢዝነስ ኔትዎርኪንግ ስራዎች ለሃገራችን የፖሊሲ አመንጭ አካላት ጥሪ የሚቀርብበት መሆኑን የገለጹት ዋና ጸሃፊው ትኩረት የሚሹ የቢዝነስ ጉዳዮች የሚጠየቁባቸው፡በንግድ ትርኢቶቹ የሚሳተፉ ሁሉ ያሉባቸውን ችግሮች ለፖሊሲ አውጭዎች የሚቀርቡባቸው የውይይት መድረኮች እንደሚኖሩም ጠቅሰዋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ በ2016 ዓ.ም የሚያካሂዳቸው ሶስቱ የንግድ ትርኢቶች፡ የንግዱን እና የአገልግሎት ዘርፉን የሚያካትተው 26ተኛው አዲስ ቻምበር አለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ፤14ተኛው አዲስ ቻምበር አለም አቀፍ የግብርና እና የምግብ ንግድ ትርኢት፤ እንዲሁም 6 ተኛው የማኑፋክቸሪንግ እና ቴክኖሎጂ አለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ናቸው፡፡