የንግድ ምክር ቤቶች የአባሎችን ጥቅም ማስጠበቅ ቀዳሚ ትኩረታቸው ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገለጸ

የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከክልል ምክር ቤቶች ጋር የልምድ ልውውጥ አካሂዷል፡፡
በልምድ ልውውጡ ከአማራ ፡ከኦሮምያ እና ከሲዳማ ክልል ንግድ ምክር ቤት ተወካዮች እንዲሁም የዱቄት ማቀነባበር፡የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች እንዲሁም፤የወተት እና የወተት ተዋጽዎ አምራች ማህበር ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
ከ75 አመት በላይ ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በዘመናዊ አሰራሮች በመታገዝ ለንግዱ ማህበረሰብ ምቹ የንግድ ከባቢ እንዲፈጠር እራሱን በማደራጀት አገልግሎት ሲሰጥ በቆየባቸው አመት ውስጥ ያካበተውን ልምድ ከዚህ በፊትም ለሌሎች ሲያጋራ ቆይቷል፡፡
የንግድ ምክር ቤቶች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአባልነት አሰራር የሚከተሉ በመሆናቸው ቀጣይነታቸው ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ አባላት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ በወቅቱ እንዲከፍሉ እና ቁጥራቸውም እንዲጨምር ማድረግ ምክር ቤቶችን በተመሳሳይ የሚፈትን ሲሆን፤ለዚህ ደግሞ አባላት ከምክር ቤቶቻቸው የሚያገኙት አገልግሎት የተደራጀ መሆን እና ጥቅማቸውን የሚስጠብቅ መሆን እንዳለበት ተነስቷል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በተለያዩ ዘመናት የሚገጥሙትን ችግሮች ከመፍታት አንጻር ሰፊ ልምድ ያለው በመሆኑ ይህ አጋጣሚ ልምድ ለመቅሰም ጥሩ እድል እንደሆነ ያነሱት ተሳታፊዎች፡በምክር ቤቱ የተለያዩ የስራ ክፍሎች የቀረቡትን ልምዶች መነሻ በማድረግ ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል::
ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከልም የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የአባላት ቁጥር ከማብዛት እንዲሁም ከክፍያ አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የሚከተለውን አሰራር ፡የንግዱን ማህበረሰብ ጥያቄዎች የሚገጥሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ምላሽ እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር፡የንግዱን ማህበረሰብ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ሚና በግልጽ እንዲታወቅ ከማድረግ አንጻር እንዲሁም ከዲጂታል አሰራሮች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ከተነሱት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው::
ለጥያቄዎቹም ከሚመለከታቸው የምክር ቤቱ የስራ ክፍሎች ምላሽ ተሰቷል፡፡
ተሳታፊዎቹ አክለውም እንዲህ አይነት የልምድ ልውውጥ ሰፊ እውቀት የሚገኝበት መሆኑን ከግምት በማስገባት ሌሎች የክልል ምክር ቤት የቦርድ አመራሮችም እድሉን ሊያገኙ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ የነጋዴዎችን አቅም ለማሳደግ የሚያግዙ የሃገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሃገር የልምድ ልውውጦችን ማካሄድ ሲሆን ከክልል ምክር ቤቶች ጋር የተካሄደውም የልምድ ልውውጥ የዚሁ ክፍል መሆኑ ተነግሯል፡፡