የንግድ ዘርፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ቅንጅት ያስፈልጋል ተባለ

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ንግድ ተሳትፎን ለማሳደግ የመንግሥትና የግል ዘርፍ ቅርበትና ትብብር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው በአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዘጋጅነት በተካሄደው 6ኛው ዙር የመንግሥትና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክ ላይ ነው።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አበበ ጉርሜሳ (ኢ/ር) እንደገለጹት፣ የግልና የመንግሥት ዘርፍ በቅርበት መሥራት የሀገሪቱን የዓለም አቀፍ ንግድ ተሳትፎ ለማሳደግ ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በመድረኩ የንግዱ ማኅበረሰብ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግና በተለይም የአምራች ዘርፉን ለመደገፍ ተጨማሪ ሥራዎች እንዳሉ ተጠቁሟል።

በተጨማሪም በዕለቱ በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትና በአፍሪካ የኤሌክትሮኒክ ንግድ ቡድን መካከል የገበያ ትስስርን ለማሳደግ፣ የዲጂታል ግብይትና መድረኮችን ለመደገፍ እንዲሁም አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሟል።

በመድረኩ ከ100 በላይ የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የልማት አጋሮች፣ የመገናኛ ብዙኃንና የማኅበራት አመራሮች ተሳትፈዋል።