የማዕከሉ መከፈት የንግዱ ሕ/ሰብ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሥርአት ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ ያሳድጋል ተብሏል፡፡
የንግድ ም/ቤቱ ዋና ጸሐፊ መሠረት ሞላ(ዶ/ር) የግሉ ዘርፍ አባላት ሃብት እና ወጪ በመቆጠብ፤ በአካባቢ ላይ የሚያደርሱትን ተጽእኖ እንዲቀንሱና በምርት እና አገልግሎት ጥራት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማዕከሉ ትልቅ ድጋፍ ያበረክታል ሲሉ በመክፈቻ ሥነሥርአቱ ላይ ተናግረዋል፡፡
ዛሬ ላይ መንግሥት በታዳሽ ሃይል የታገዘ እና ከካርበን ልቀት ነጻ የሆነ ኢኮኖሚ ለማሰፋፋት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል ፡፡
ስለዚህ አዲስ ቻምበር የንግዱ ሕ/ሰብ አረንጓዴ ፟ተኮር ወደ ሆነው የዘመናችን ኢኮኖሚ ሽግግር ጋር አብሮ እንዲጓዝ ለማገዝ በማሰብ የአቅም ግንባታ ማዕከል ከፍቷል ፡፡
ማእከሉ በዘላቂነት አገልገሎቱን መስጠት እንዲችል ሁሉም ባለድርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚ/ር ተወካይ የሆኑት አቶ እስማኤል መሐመድ መንግሥት ለአካባቢ እንክብካቤ ትኩረት ስጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ለፕሮጀክቱ ተፈፃሚነት ሚኒስቴሩ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የአየር ለውጥን የሚቋቋምና ቀጣይ የሆነ አገራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ የአረንጓዴ ማንዩፋክቸሪንግ ስትራቴጂ አንዱ ነው ብለዋል፡፡
GIZ የተሰኘው የጀርመን የልማት ድርጅት ተወካይ አና ዋልድማን በበኩላቸው የማዕከሉ መከፈት ላኪዎች በተለይ ምርታቸው በአውሮጳ ተቀባይነት እንዲያገኝ ይረዳል ብለዋል፡፡
ድርጅታቸው ለቡና አቅራቢዎች ፤ለጨርቃጨርቅ እና አልባሳት አምራቾች ከአካባቢ ተጽዕኖ ነጻ ወደ ሆነ የአመራረት ሥርአት ሸግግር እንዲያደርጉ ድጋፍ እየስጠ ነው ብለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ፤ከሚድሮክ ኢትዮጵያ ፤ከደርባ ስሚንቶ ፋብሪካ፣ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ የተወከሉ ባለሙያዎች ብከለትን በመቀነስ ከአካባቢ ጋር ስምም በሆነ መልኩ የሚያከናውኑትን የአመራረት እና አገልግሎት አሰጣጥ ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለ150 ትላልቅ የግል ኢንተርፕራይዞች ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፕሮጀክቱ ከጂአይዜድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ለ አንድ አመት በአዲስ ቻምበር በኩል የሚተገበር ይሆናል።
በካፒታል ሆቴል በተከናወነው የፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐግብር ላይ የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሐራ መሐመድን ጨምሮ የቦርድና የማኔጅመንት አባላት ፣የመንግሥት ሀላፊዎች እና የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዬች ተገኝተዋል ።