ንግድ ምክር ቤቱ የሥራ ፈጣሪዎችን ለማገዝ ያለመውን የኢንኩቤተር ማዕከል አቋቋመ::

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎችን (Start-ups) በቴክኒክ፣ በእውቀትና በገንዘብ ለመደገፍ የሚያስችለውን የቢዝነስ ኢንኩቤተር ማዕከል ማቋቋሙን የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ አቶ ሽበሺ ቤተማርያም ለኢትዮ የንግድና ኢንቨስትምንት መድረክ ተናገሩ፡፡

ማዕከሉ ለአራት አመታት 500 አዳዲስ ሥራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ እንዲችል 29 ሚሊዮን ብር በጀት ከምክር ቤቱ ተመድቦለታል፡፡

የበጀቱ መጠንም ወደፊት ጭማሪ እንደሚደረግበትና ለመጀመሪያ አመት ተግባራት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ማቋቋሚያ በጀት ሆኖ ፀድቋል፡፡

የቢዝነስ ኢንኩቤተር ማዕከላት በተለያዩ አገራት ገቢራዊ እንደሆነው ሁሉ በኢትዮጵያም በተመሳሳይ የሃሳብ ማፍለቂያዎችና ለግዙፍ ኢንዱትሪዎችም እንደመነሻ የሚያገለግሉ መሆናቸውን አቶ ሽበሺ አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያም እነዚህ ማዕከላት መበራከት እንዳለባቸውም አቶ ሽበሺ ይሞግታሉ፡፡

ማዕከሉ የሥራ ፈጣሪዎቹን የቢዝነስ ሃሳቦች ድጋፍ በማድረግ ሃሳቦቻቸውን የሚያበለፅጉና የሚረዱ አሰልጣኞችን ጨምሮ በርካታ ለሥራ ፈጣሪዎቹ የሚያግዙ ሁኔታዎች የተሟሉለት ፅ/ቤትም ይኖረዋል፡፡

የሥራ ፈጣሪዎቹም በሚያቀርቧቸው የቢዝነስ ሃሳቦች፣ በሚፈጥሯቸው የሥራ እድሎችና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ በሚኖራቸው አበርክቶ መስፈርትነት እንደሚወዳደሩም አቶ ሽበሺ አንስተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *