የእሳት አደጋው በተከሰተበት መርካቶ ሸማ ተራ የተገኙት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ የቢሮው ከፍተኛ አመራሮች ፤ የአዲስ ቻምበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሽንቁጤ እና ሌሎች የንግድ ምክር ቤት ከፍተኛ ኃላፊዎች ቦታው ድረስ በመገኘት የጉዳቱን መጠን የተመከለቱ ሲሆን የጉዳቱ ሰለባ የሆኑትን አጽናንተዋል፡፡
የአደጋው መጠን እንዳይጨምር በቁጥጥር ስር እንዲውል ርብርብ ያደረጉ አካላትን ያመሰጉነት ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ የደረሰው ጉዳት በእጅጉ እንዳሳዘናቸውና የከተማ አስተዳደሩ የአደጋውን መንስኤ በማጣራት ለህዝብ የሚያሳውቅ መሆኑን እና የንግዱ ማህበረሰብ ሌሎች መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ መርካቶ በኢትዮጵያ ትልቁ የገበያ ማዕከል መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ መሰንበት በበኩላቸው የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል፡፡ አክለውም በቦታው የንግድ ስራ ያከናውኑ የነበሩ ነጋዴዎች በአደጋው ከገጠማቸው ጉዳት አገግመው በቶሎ ወደ ስራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡ በመሆኑም እሳቸው የሚመሩት ንግድ ምክር ቤት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር አቅሙ በፈቀደው መጠን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መርካቶ የአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን የመላው አገሪቱ የኢኮኖሚ እምብርት ነች ያሉት ወ/ሮ መሰንበት ተጎጂዎችን ማገዝ ላይ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡