የአዲስ ቻምበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ መሃመድ ከአርመን አምባሳደር ጋር ተወያዩ

የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ መሃመድ የኢትዮጵያና የአርመንን ታሪካዊ የንግድ ግንኙነት ይበልጥ ለማነቃቃት በኢትዮጵያ የአርመን አምባሳደር ሳሃክ ሳርክስያንን  በምክር ቤቱ ዋና ጽሕፈት ቤት ተቀብለው ተወያይተዋል፡፡

ወ/ሮ ዘሃራ መሃመድ የአርመን ኩባንያዎች ያላቸውን የንግድና የኢንቨስትመንት አቅም ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ከሀገር ውስጥ ነጋዴዎች እንዲሁም ከመሰል ምክር ቤቶች ጋር ጠንካራ ትስስር መፍጠር በሚችሉባቸው ዕድሎች ዙሪያ ከአምባሳደሩ ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ዘካሪያስ አሰፋ በበኩላቸው፣ ምክር ቤቱ ከተመሠረተበት  ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 79 ዓመታት ፖሊሲ ላይ ለውጥ እንዲመጣ፡ ለአባላቱ የንግድ ድጋፍ፣ ስልጠናና ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት አገልግሎቶችን በመስጠት ረገድ ያከናወናቸውን ተግባራት አብራርተዋል፡፡ በምክር ቤቱ ታሪክም አርመናውያን ነጋዴዎችና ባለሙያዎች ለንግድ ምክር ቤቱ መመስረትና ለሀገሪቱ የንግድ ዘርፍ መዘመን ያበረከቱትን ታሪካዊ አስተዋጽኦ በከፍተኛ አክብሮት እንደሚያስታወስ በውይይቱ ተነስቷል፡፡

የአርመን አምባሳደር ሳሃክ ሳርክስያን በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው  አምባሳደር መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ኤምባሲያቸው ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የሚገኝ ብቸኛው የአርመን ኤምባሲ መሆኑንና ይህም ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሳይ አስገንዝበዋል. አምባሳደሩ በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ መጠን  አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንን እምቅ አቅም ለመጠቀምና ግንኙነቱን አዲስ ምዕራፍ ላይ ለማድረስ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት በጋራ ለመስራት ከተነሱት ነጥቦች መካከል በሁለቱ ሃገራት ነጋዴዎች መካከል የንግድ ትስስር ለመፍጠር አዲስ ቻምበር እና የአርመን ኤምባሲ እንዲሁም መሰል ምክር ቤቶች በትብብር መስራትን አስመልክቶ፡በሁለቱ ሀገራት መካከል የንግድ ግንኙነቱን ለማሳደግ በኢትዮጵያ እና በአርመን ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶችን ማደራጀት እና የንግድ ልዑካንን በማሰማራት፡እንዲሁም  አርመን ኢትዮጵያን ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት መግቢያ በር አድርጋ እንደምትመለከት በመጥቀስ፣ የአርመን ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው በማምረት ምርቶቻቸውን ወደ ተለያዩ ሀገራት እንዲልኩ ለማስቻል የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በማጠቃለያውም ሁለቱም ወገኖች የተነሱትን የትብብር ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በጋራ ለመስራት ሙሉ ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን  አምባሳደር ሳሃክ ሳርክስያን በአርመናውያን እና በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን የዘመናት ታሪካዊ ትስስር የሚያሳይ መጽሐፍ ለፕሬዝዳንቷ በስጦታ አበርክተዋል፡በተመሳሳይም የአዲስ ቻምበርን ታሪክ የያዘ መጽኃፍ ወ/ሮ ዘሃራ ለአምባሳደር ሳሃክ በስጦታ አበርክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትና አርመናውያን ታሪካዊ ትስስር ያላቸው ሲሆን በ1939 አ.ም ምክር ቤቱ ሲመሰረት ጀምሮ እስከ 1953 አ.ም ድረስ የመጀመርያው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕረዚደንት ሆነው ያገለገሉት ሚስተር ቢ.ባባያ ናቸው፡፡

wpChatIcon
wpChatIcon