19 አባላትን የያዘው የህንድ የንግድ ልኡካን ቡድን በኢትዮጵያ ከሚገኙ የንግዱ ማህበራሰብ አባላት ጋር በጋራ መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መከሩ ፡፡

የግሎባል ህንድ ቢዝነስ ግሩፕ እና የህንድ ዓለም አቀፍ ንግድ ምክር ቤት ኢንዱስትሪ እና ግብርና አባላት በኢትዮጵያ ያለውን የቢዝነስ እድል ለመገንዘብ መምጣታቸውን ገልፀዋል ፡፡
በፋርማሲቱካል ፣ ከሶሞቲክስ ፣ ፕላስቲክ ምርት ፣ የግብርና ፣ማሽነሪ እና ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ 19 የህንድ ኩባንያዎች በተመሳሳይ ዘርፍ ላይ ከሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎች ጋር በጋራ ሊሰሩ በሚችሉበት መንገድ መክረዋል ፡፡
የአዲስ ቻምበር ምክትል ዋና ፀሀፊ አቶ ዘካሪያስ አስፋ የንግድ ለንግድ ውይይቱ ሲጀመር ለልኡካኑ ባደረጉት ገለፃ ንግድ ምክር ቤታቸው አንጋፋና ጠንካራ ንግድ ምክር ቤት መሆኑን ገልፀው የንግድ ግንኙነቱ ወደ ተግባር እንዲለወጥ ተቋማቸው አበክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ቻምበር ያነጋገረቻቸው የህንድ የንግድ ልኡካን አባላት በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያለውን የቢዝነስ እድል ለማየት እንዲሁም በኢትዮጵያ ያሉ ምርቶችን ወደ ህንድ ማስገባት እንዲሁም የህንድ ምርቶችን ለመላክ ያለውን እድል ለማየት መሆኑን ገልፀዋል ፡፡
ኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎች በበኩላቸው በአካል ተገናኝቶ መነጋገሩ በኦንላይን እና በስልክ ከመነጋገር የበለጠ እምነት እንደሚያሳድር ገልፀዋል ፡፡
አዲስ ቻምበር 17 ሺ አባላት ያሉት ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ300 በላይ የሚሆኑት የውጭ አገር ኩባንያዎች መሆናቸውን በውይይቱ ላይ ለማወቅ ተችሏል ፡፡