የኢትዮጵያዊያን ኩባንያዎች የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠና ገበያን እንዲጠቀሙበት ለማድረግ እየሠራ መሆኑን አዲስ ቻምበር ገለፀ።

ቀጠናው ለግሉ ዘርፍ በተለይም ለአነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ይዞ የመጣው እድልና የንግድ ምክር ቤቶች ሚና በሚል የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል ።

 

በፈረንሣይ የልማት ድርጅት ማለትም በኤክስፐርቲዝ ፍራንስ እና በኤኮ ትሬድ ፕሮጀክት አዘጋጅነት በተሰናዳው የፓናል ውይይት ላይ የአዲስ ቻምበር ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ ካሳሁን ማሞ የንግድ ቀጠናው ለኩባንያዎችና ለአባላት ያለውን እንድምታና ንግድ ምክር ቤቱ በአፍሪካ ሐገራት መካከል የንግድ ትስስር እንዲጠናከር እያከናወናቸው ያሉትን ስራዎች በፓናል ውይይቱ ላይ ማብራሪያ ሠጥተዋል።

 

የአለም ንግድ ድርጅት ከተመሰረተ በኋላ በቅርቡ እውን የሆነው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የአለማችን ግዙፉ ቀጠና ነው ያሉት የአዲስ ቻምበር ምክትል ዋና ፀሐፊው ስምምነቱ የገበያ አድማስን የሚያሰፋ፣ ታሪፍን በመቀነስ በሐገራት መካከል ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያሳድግ፤የፖሊሲ ውህደትንና የህጎች መጣጣምን የሚጠይቅ በመሆኑ ሸቀጦችና አገልግሎቶች እንደልብ መዘዋወር ይችላሉ ብለዋል፡፡

 

እንደ አቶ ካሳሁን ገለፃ አሁን ያለው 1.4 ቢሊዮን የአፍሪካ ስነ ሕዝብ በ2050 ወደ 2.5 ቢሊዮን እንደሚያድግና ይህም ለኢትዮጵያውያን ኩባንያዎችና ስራ ፈጣሪዎች ግዙፍ እድሎችና ገበያን ይፈጥራል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል ፡፡

የአዲስ ቻምበር አባል ኩባንያዎች እና መላው የአዲስ አበባ የንግዱ ህብረተሠብ ስለአህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጠናው እና አተገባበሩ ላይ ያላቸውን ዕውቀት ለማሳደግ እና አቅማቸውን ለማጠናከር እንዲሁም የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየተሠሩ ያሉ ተግባራት ከአጋር አካላት ጋር መሆን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የሀገራችን የግሉ ዘርፍ በተለይም የአነስተኛ፤ ጥቃቅንና መካከለኛ የንግድ ኩባንያዎች ያሉባቸውን ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች በመፍታት በነፃ ንግድ ቀጠናው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አዲስ ቻምበር አበክሮ እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

 

በፖሊሲ ደረጃ ያሉና በአብዛኛው ከንግድ ከባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር የተያያዙትን በተመለከተ በየጊዜው እየታዩ ማስተካከያ የሚደረግባቸውና አሁንም እየተደረገባቸው እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ካሳሁን በኩባንያ ደረጃ ያሉ ችግሮች ከአደረጃጀት፣ከአሰራርና ከሰው ሀይል ጋር ተያይዘው የሚታዩ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡

 

በዚህ ረገድ አዲስ ቻምበር በአፍሪካ ሐገራት ካሉ የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች ጋር ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ተጠቅሞ አባል የአዲስ አበባ ኩባንያዎች ጥራት ያለውና ደረጃውን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት በተሳለጠ መንገድ እንዲገበያዩ የገበያ ትስስር እየፈጠረና ይህንንም ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሐላፊው አስረድተዋል ፡፡

 

በአጠቃላይ የሀገራችን የግሉ ዘርፍ አቅም ሊጠናከር እንደሚገባና መንግሥስትን ጨምሮ የንግድ ምክር ቤቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ ለነገ የሚባል ባይሆን ይመረጣል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

የነጻ ንግዱን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመተግበር የፋይናንስና ኢኮኖሚ ተቋማትን አሠራር በይበልጥ ማሻሻል፣ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መገንባት፣ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን አሁንም መቃኘት፣ የፋይናንስ አና የመስሪያ ቦታ አቅራቦትን ማሻሻል ፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀትንና የንግድ ድጋፍ አገልግሎትን ማጠናከር፣ የግንዛቤ ማስፋፊያ ስራዎች በስፋት ማካሄድ ፣የሎጀስቲክስና የመሠረተ ልማት አውታሮችን መዘርጋት እና የአፍሪካ ሐገራት መንግስታት ቁርጠኝነት በተጨባጭ መኖር የሚሉት ምክረ ሐሳቦች በአዲስ ቻምበር ቀርበዋል።

 

በፓናል ውይይቱ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትን ጨምሮ የፓን አፍሪቃ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤትና CAWE ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን የአዲስ ቻምበር አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማት እና ጥሪ የተደረገላቸው አጋር አካላት ተገኝተዋል ።

 

#አዲስ ቻምበር፤ ከ1939 ዓም ጀምሮ የንግዱ ማህበረሰብ አገልጋይ እና ድምፅ