የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) ከኔዘርላንዱ የልማት ድርጅት (SNV) እና ከGIZ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ታሪካዊው የአረንጓዴ ኢንቨስትመንት ፎረምና ኤግዚቢሽን ጷጉሜ 3 ቀን 2018 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል እንደሚካሄድ አስታወቀ።
በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫው የቻምበሩ ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ ካሳሁን ማሞ እና የSNV ፕሮጀክት ማኔጀር ሔለን ጌታሁን እንደገለፁት፣ መድረኩ በዘላቂ ኢኮኖሚ፣ ታዳሽ ኃይል እና አካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ ነው።
በሁነቱ ላይ ከ100 በላይ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና ስራ ፈጣሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን፣ የካርቦን ቅነሳና የአረንጓዴ ፋይናንስ ጥናቶች ይቀርባሉ ተብሏል።
በተጨማሪም አረንጓዴ ቢዝነስ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበትና የወጣቶችና ሴቶች ስራ ፈጠራ የሚበረታታበት መድረክ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
