አዲስ ቻምበር ከቤልጅየም እና ሉግዘምበርግ የንግድ ምክር ቤት ጋር በጋራ ለመስራት የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ ።

ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች ለማሳደግ እና ለማስተዋወቅ የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል ።

የኢትዬ ቤልጂየም ታላቅ የንግድ መድረክ በስኬት ተጠናቀቀ ።

በቤልጂየም እና ሉግዘምበርግ የንግድ ፣ኢንዱስትሪና ግብርና ምክር ቤት ( CBL-ACP) የተመራ የንግድ ልኡካን ቡድን  ከአዲስ ቻምበር አባል ኩባንያዎች እና ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር ሲያካሂድ የነበረውን የንግድ ለንግድ ውይይት አጠናቋል ።

ከ 10 በላይ ትልልቅ አለም አቀፍ ኩባንያዎችን ያካተተው የንግድ ልዑኩ ለ3 ቀናት በአዲስ አበባ በመገኘት የተለያዩ የቢዝነስ እድሎችን ያማተረ ሲሆን  ልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት መሠረተ ልማቶችንም ጎብኝቷል ።

የንግድ ልኡኩ በማጠቃለያው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች ለማሳደግ እና ለማስተዋወቅ የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ስምምነት በአዲስ ቻምበርና በቤልጂየሙ ንግድ ምክር ቤት መካከል በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ተፈርሟል ።

የጋራ መግባቢያ ሰነዱን የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሐራ መሐመድ እና የቤልጅየም እና ሉግዘምበርግ ንግድ ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ሚስተር ቶማስ ዴቡል ፈርመውታል ።

በፊርማ ስነስርአቱ እና በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ በኢትዮጵያ የቤልጂየም አምባሳደር አኒሌስ ቨርሲቼይል(ዶ/ር) እና የአዲስ ቻምበር ተ/ዋና ፀሐፊ አቶ ዘካሪያስ አሠፋ  ተገኝተው የማጠቃለያ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

አምባሳደር አኔሌ ቨርሲቼይል(ዶ/ር) በንግግራቸው እንዳሉት የቤልጂየም የንግድ ልኡካን ቡድን  በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሠማራትም ሆነ የንግድ እድሎችን ለመጠቀም ከአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አባል ኩባንያዎችም ሆነ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን በቂ መረጃ ማግኘታቸውን ጠቁመው በአጠቃላይ የንግድ ለንግድ ግንኙነቱና ውይይቱ ስኬታማ መሆኑን ተናግረዋል ፡ ፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት/ አዲስ ቻምበር/ ተ/ዋና ፀሀፊ አቶ ዘካሪያስ አሰፋ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ መጠን ከ 350 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ጠቅሰው ሁለቱም ሀገራት ካላቸው እምቅ አቅም አንፃር አሀዙን ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል ፡ ፡

ሁለቱ ንግድ ምክር ቤቶች በየሐገሮቻቸው ያለውን ንግድና ኢንቨስትመንት ለማበረታታት ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ገልፀው ሁለቱ ንግድ ምክር ቤቶች በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል፡ ፡

የቤልጅየም ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት እድል እንደሚጠቀሙና በቀጣይም በአዲስ ቻምበር በኩል የኢትዮጵያ ባለሐብቶች በተለይም የአዲስ ቻምበር አባል ኩባንያዎች  በቤልጅየም እና ሉግዘምበርግ በመገኘት የንግድ ለንግድ ግንኙነት እንዲያደርጉ ምክር ቤታቸው ምቹ ሁኔታ እንደሚመቻች አቶ ዘካሪያስ ተናግረዋል፡ ፡

የቤልጂየምና ሉግዘምበርግ ንግድ ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ቶማስ ዴቡል በበኩላቸው በአዲስ አበባ የተገኙት ትልልቅ የቤልጂየም ባለሀብቶች በጨርቃጨርቅ ፣በምግብና አግሮ ፕሮሰሲንግ ፣በፋርማሲቲካል፣ በታዳሽ ሀይል፣  እና በአይሲቲ ዘርፎች ይበልጥ ለመሠማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልፀዋል ፡፡

ቤልጂየም የአውሮፓ ህብረት ዋና መቀመጫ ስትሆን እኤአ በ2024 የሀገሪቱ  ጥቅል ሀገራዊ የምርት መጠኗ ከ 650 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

እኤአ ከ ጁን 1-4፣ 2025 ለ3 ቀናት የቆየውን ታላቅ የኢትዮ ቤልጂየም የንግድ መድረክ በአዲስ ቻምበር ፣ በአዲስ አበባ የቤልጂየም ኤምባሲ፤  በቤልጅየም እና ሉግዘምበርግ ንግድ ምክር ቤት፣ በኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ ብራሰልስ የሚገኘው በኢትዬጲያ ኤምባሲ እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የጋር ትብብር የተዘጋጀ ነው።