አዲስ ቻምበር አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ አደረጃጀቱን በክፍለከተማ ደረጃ መዘርጋቱን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት/ አዲስ ቻምበር/ በከተማዋ ከ482 ሺህ በላይ የጸና ንግድ ፈቃድ ያላቸውን ነጋዴዎች አባል ለማድረግና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች መዋቅሩን መዘርጋቱን አስታውቋል፡፡

አንድ ሰብሳቢን ጨምሮ ዘጠኝ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካይ በየክፍለ ከተማው በአመራርነት የመደበ ሲሆን የምክር ቤቱን ስራዎችን የሚያስተባብሩ ሰራተኞች እንደሚመደቡ ተገልጿል፡፡

የአዲስ ቻምበር የቦርድ አባላትና የአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ሰብሳቢዎች በአደረጃጀቱና በስራዎች ዙርያ ምክክር አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የአዲስ ቻምበር ፕረዚደንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ እንደገለጹት የክፍለ ከተማ አመራሮች የንግዱን ማህበረሰብ በቅርበትና በታማኝነት በማገልገል በከተማዋ የተደራጀ የንግድ ማህበረሰብ ድምጽ እንዲኖርና የንግዱን ማህበረሰብ መብትና ጥቅም የሚያስከብር ሁኔታ እንዲፈጠሩ አሳስበዋል፡፡

አዲሱ አደረጃጀት በቅርቡ ወደ ትግበራ እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን አባላቱን በስፋት ለማሳተፍና አገልግሎቱን በማዘመን ተደራሽ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት/ አዲስ ቻምበር/ ሪፎርም በማካሄድ ላይ ሲሆን በዋናነት የአባላት ተደራሽነትን ማስፋት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡