ሴቶች ከመብቶቻቸው ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ችግራቸውንም መፍታት ወሳኝ መሆኑም ተጠቁሟል።
የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የሴቶች ቀንን አስመልክቶ ስራ ፈጣሪ ሴቶችን ማብቃት ለተወዳዳሪነታቸው በሚኖረው አስተዋጽኦ ላይ በማተኮር የውይይትና የተሞክሮ ልዉዉጥ መድረክ አካሂዷል፡፡
አዲስ ቻምበር የዓለማቀፉን የሴቶች ቀን /ማርች 8/ ምክንያት በማድረግ ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የም/ ቤቱ ፕሬዝደንት ወ/ሮ ዘሐራ መሀመድ ባስተላለፉት መልዕክት ሴቶች በኢንቨስትመንት እና በሥራ ፈጠራ ላይ በስፋት እንዲሳተፉ አበረታች የፖሊሲና የአሰራር እርምጃዎች ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
መንግሥት ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ትኩረት መስጠቱ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ሴቶች በስራ ፈጠራ ዘርፍ ላይ ያላቸውን አነስተኛ ተሳትፎ ለማሳደግ በሴቶች ላይ ያተኮሩ ፖሊሲዎችን በመፈተሽ ማበረታቻዎቸን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ፕሬዝደንቷ አሳስበዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ከአዲስ አበባ ሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተገኙት ወ/ሮ በረከት በቀለ በበኩላቸው ሴቶች በአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መንግሥት የተለያዩ የሕግ እና የፖሊሲ እርምጃዎችን ወስዷል ብለዋል፡፡
ነገር ግን የሴቶች በኢንቨስትመንት በተለይም በስራ ፈጠራ ዘርፍ ላይ ያላቸው ተሳትፎ በጣም አነስተኛ መሆኑን አሰታውሰው ይህንን እውነታ ለማሻሻል መ/ቤታቸው አዲስ ቻምበርን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
ሴት ስራ ፈጣሪዎች ስራቸውን ለማሳደግም ሆነ ለማስፋት የብድር አቅርቦት አንዱ ማነቆ መሆኑን ከግምት በማስገባት በተመጣጣኝ ወለድ ብድር የሚያገኙበት መንገድ እና ተያያዥ የአቅም መገንብያ እገዛዎች ማስፈለጋቸውን ከግምት በማስገባት በሴቶች የተቋቋመው እናት ባንክ ለሴት ስራ ፈጣሪዎች ያዘጋጀውን አገልግሎት ወ/ሮ ሃብታምነሽ አስፋው የባንኩ የሴቶች የባንክ አገልግሎት ሃላፊ አብራተዋል፡
በሥነስርዓቱ ላይ ስኬታማ የሆኑ ሴት የቢዝነስ መሪዎች እና ሥራ ፈጣሪዎች ተሞክሯቸውን ያቀረቡ ሲሆን በተለይ ሴቶችን በሥራ ፈጠራ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዙሪያ ያሉ ዕድሎች እና ተግዳሮቶችን እንዲሆኑም ማነቆ የሆኑ ፖሊሰዎች እና አሰራሮች የጠቆሙ ሲሆን የመፍትሔ ሃሳቦችንም ሰንዝረዋል፡፡
ልምዳቸውን ካካፈሉት ውስጥ አትሌትና ነጋዴ ጌጤ ዋሚ፣ ወ/ሮ ሃይማኖት ተስፋዬ የኢቴል ኢቨንት እና ኮሚኒኬሽን መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ፣ ወ/ሮ ሰሎሜ ዳኛቸው የኢንተርየር ዲዛይነር እና ወ/ት ሳምራዊት ታረቀኝ የቴክኖሎጂ ባለሞያ ሲሆኑ ሁሉም በተሰማሩበት የስራ መስክ ያላቸውን ጥንካሬ ለሌሎች ሴት ስራ ፈጣሪዎች አጋርተዋል፡፡
የፓናል ውይይቱን ወ/ሮ ትህትና ለገሰ የዋሪት ሙሉጥላ ኢንተርናሽናል ማኔጂንግ ዳይሬክተር መርተውታል።
ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች እና አሰተያየቶች የተሰጡ ሲሆን በአቅራቢዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
አዲስ ቻምበር ከዳኒሽ ኢንዱስትሪ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የዘንድሮው የዓለም ሴቶች ቀን ‘Women In Entrepruenrship’ በሚል መሪ ሃሳብ መሆኑ ታውቋል ፡፡