ተቋሙ በዚህ ገበያ ላይ መመዝገቡን ይፋ ያደረገው ከኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ጋር በመተባበር ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 18፤ 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባው ስካይላይት ሆቴል በሰጠው የጋራ መግለጫ ነው።
እስካሁን በሀገሪቱ የመጀመሪያውና ብቸኛው የተደራጀ የካፒታል ማርኬት የሆነው እና በመንግሥትና በግል አጋርነት የተመሠረተው የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ላይ በይፋ ተመዝግበው ተሳታፊ የሆኑት ሦስት የፋይናንስ ተቋማት ብቻ ነበሩ።
የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ በይፋ ሥራ መጀመሩ በተበሰረበት በጥር 2017 ዓ.ም.፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በገበያው ላይ መመዝገቡ የተገለጸው ወጋገን ባንክ ነበር።
ከወጋገን ባንክ ምዝገባ ስድስት ወራት በኋላ ገዳ ባንክ፣ ከአንድ ወር በፊት ደግሞ አዋሽ ባንክ በዚሁ ገበያ ላይ መመዝገባቸው ይፋ ተደርጓል።
ኢትዮ ቴሌኮም አራተኛ ተቋም ሆኖ በሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ላይ ከመመዝገቡ አስቀድሞ 100 ሚሊዮን መደበኛ አክሲዮኖቹን ለሽያጭ ገበያ አውጥቶ ነበር።
ኩባንያው ባለፈው ሚያዝያ ወር ባወጣው መግለጫ ለአራት ወራት ያህል ክፍት ሆኖ በቆየው በዚህ የሽያጭ ሂደት ለሽያጭ ካቀረበው የ10 በመቶ የኩባንያው ድርሻ ውስጥ 10.7 ሚሊዮን መደበኛ አክሲዮኖች ብቻ የተሸጡ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 89.3 ሚሊዮን አክሲዮኖች ግን ሳይሸጡ ቀርተዋል።
አክሲዮን ከገዙ ዜጎች ውስጥ 45,336 የሚሆኑት “የባለቤትነት ማረጋገጫ”ሂደታቸውን ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቃቸው በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
