የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በጋራ ያዘጋጄዉ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ዘገባ ስልጠና ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለተወጣጡ ጋዜጠኞች መስጠት ተጀምሯል፡፡
ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ስልጠናዉን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ሚዲያና የሚዲያ ባለሙያዎች ለሃገር እድገትና ህልዉና ካላቸዉ ከፍተኛ ሚና አንጻር የሚሰሯቸዉን የሚዲያ ስራዎች በሙያዊ ዲስፕሊን ፣ በእዉቀትና ለሃገርና ለህዝብ በወገንተኝነት መሆን አለበት ብለዋል፡፡
በሚዲያዎቻችን በኩል በተለይም በቢዝነስና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ዘገባ ዙሪያ ክፍተቶች መኖራቸዉን ያነሱት ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም ይህንን ክፍተት ለመቅረፍም በተከታታይ ስልጠናዎችን ለመስጠት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለዉ አረጋግጠዋል፡፡ ጋዜጠኛ እንደ ወታደር ነዉ ያሉት ዶ/ር ፍጹም የሚዲያ ባለሙያዎች መረጃ መታጠቅ አለባቸዉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመጋፈጥ መስራትም ከሙያዉ ይጠበቃል ነዉ ያሉት፡፡ በመንግስት በኩል ለመገናኛ ብዙሃን የተሻለ ሁኔታን ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በበኩላቸዉ ምክር ቤቱ የጋዜጠኖችን አቅም በማሳደግ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም የሃገሪቱን የቢዝነስና የኢንቨስትምንት እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍና ጥራት ያለዉና ሚዛናዊ መረጃን ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡
አዲስ ቻምበር ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የማገዝ ፣ የዉጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ እንዲጠናከር የማስቻል እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ ያሉበትን መሰረታዊ ንግድ ነክ ችግሮች ከሚመለከታቸዉ የመንግስት አካላት ጋር በመመካከር የመፍታት ተልዕኮን ይዞ እየሰራ መሆኑን ያነሱት ዋና ጸሃፊዉ መንግስትንና የንግዱን ማህበረሰብ በማስተሳሰር ዉጤታማ ስራ እየሰራ መሆኑ ጠቁመዋል፡፡
ለነዚህ ሁሉ ስራዎች ዉጤታማነት ሚዲያ ቁልፍ አቅም መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሽበሺ ቤተማርያም በቀጣይም የተጠናከረ የሚዲያ አቅም ግንባታ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
ስልጠናዉ ከተሌዩ ሚዲያዎች ለተወጣጡ 25 ጋዜጠኞች ለሁለት ቀናት የሚሰጥ ነዉ፡፡