የኮንስትራክሽን መረጃ ቋት ስርአት ሊዘጋጅ ነው

የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት የኮንስትራክሽን ዘርፍ ለብሔራዊ ኢኮኖሚ ያለው አስተዋጽኦ በሚል ርእስ የውይይት መድረክ አካሂዷል ።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚ/ር ዴኤታ ኢ/ር ወንድሙ ሴታ እንደተናገሩት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ በርካታ ችግሮች ተለይተው በሚኒስቴሩ የመፍትሔ አቅጣጫ ተቀምጦላቸዋል።
በዋናነት የመረጃ አደረጃጀት ለችግሮቹ መነሻ መሆናቸውን ያነሱት ኢ/ር ወንድሙ እያንዳንዱ ተቋራጭ ምን ያህል ግንባታዎችን እንዳከናወነ እና ውጤቱን የሚገልጽ መረጃ ሚኒስቴሩ እንደሌለው አንስተዋል ።
በተጨማሪም የሚገነቡ ግንባታዎች ዲዛይን የሚጸድቅበት መንገድም አዋጭ እንዳልሆነ ገልጸዋል። በተቀመጠው የመፍትሔ አቅጣጫ መሠረት የተጠቀሱትን ችግሮች ለመቅረፍ የኮንስትራክሽን የመረጃ ቋት ስርአት በሚኒስቴር ደረጃ እየተዘጋጀ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል ።
በሌላ በኩል ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ በመፍጠር ኢትዮጵያዊ የኮንስትራክሽን ተቋራጮች በጎረቤት ሀገራት እና በውጭ ሀገራት መሠማራት የሚያስችላቸውን አቅም መፍጠር ላይ እየተሠራ መሆኑን ኢ/ር ወንድሙ ተናግረዋል ።