የአፍሪካ አህጉር የነጻ ንግድ ቀጠና ስምምነት ትግበራ በግሉ ዘርፍ ላይ ያለው አንድምታ እና የንግዱ ሕብረተሰብ ዝግጅትና ትግበራ ምን መምሰል እንዳለበት የሚያነሳ የፓናል የውይይት መድረክ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አዘጋጅቶ ነበር፡፡
የዚህ ነፃ የንግድ ቀጠና በአጀንዳ 2063 ላይ ልዩ ቦታ ተሰጥቶት የተዋሀደች፤ የበለጸገች ሰላማዊ አፍሪካን የመፍጠር አላማ ያለው የፓን አፍሪካ ውጥን እና ራእይን ያነገበ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
የአፍሪካን አህጉር የኢኮኖሚያዊ ዉህደት የሚያስፋፋ በሰዎች ነፃ እንቅስቃሴ የሚታገዝ የእቃዎችና አገልግሎቶች አንድ ውህድ ገበያን የሚፈጥር ነው ያሉትና በመድረኩ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሃላፊ አቶ ታገስ ናቸው ፡፡
የአለም ንግድ ድርጅት ከተመሰረተ በኋላ የተመሰረተው ይህ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የአለማችን አንደኛው ግዙፍ ቀጠና ነው ያሉት ሃላፊው ስምምነቱ የታሪፍ መቀነስን፤የፖሊሲ ውህደትን የህጎች መጣጣምን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከንግዱ ህብረተሰብ አባላት በተነሳ ጥያቁ ይህ አይነቱ ታሪፍ መቀነስ የመንግስትን ገቢ በምን ያህል መጠን ሊያሳጣ ይችላል ተብሎ ለተነሳው ሀሳብ ከጉምሩክ ኮሚሽን የተወከሉት አቶ ካሳየ አየለ በዚህ ጉዳይ አሀዛዊ ቁጥር እንደሌለ ተናግረዋል::
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ አሁን ያለው 1.2 ቢሊዮን የአፍሪካ ሕዝብ በ2050 ወደ 2.5 ቢሊዮን እንደሚያድግና ይህም ግዙፍ እድሎችና ገበያን ይፈጥራል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ በግልጽ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ወገኖች በተለይም የግሉ ዘርፍ ስለአህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጠና እና አተገባበሩ ላይ ያላቸው ዕውቀት ሠፊ ሊባል የሚችል አለመሆኑን የምናየም ነባራዊ ሀቅ ነው ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ማርታ በጽሁፋቸው እንደጠቆሙት ከነጻ ንግድ ቀጠናው የሚገኙ እድሎች እንዳሉ የዘረዘሩ ሲሆን ከነዚህም መካከል ለኢትዮጰያ የወጪ ምርቶች አስተማማኝ እና ሰፊ የገበያ ዕድሎችን ይፈጥራል ብለዋል፡፡ አማራጭ ምርቶችን በተሻለ ዋጋ እንዲገኝ ያደርጋል ፤ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት (FDI inflow) እንደሚጨምርም ረዳት ፕሮፌሰሯ በጽሁፋቸው አስረድተዋል፡፡
እንዲህ አይነቱ ክልላዊ የንግድ ትስስር በተለይ የታሪፍ መቀነስን የሚያስከትል፣ የፖሊሲ ውህደትና እና የህጎች መጣጣምን የሚጠይቅ መሆኑ አንዱ ስራ የሚጠይቅ ነው ያሉት የጉምሩክ ኮሚሽን ተወካዩ ምን አልባት በኢንዱስትሪዎች ላይ የውድድር ጫና ማስከተሉ በተግዳሮትነት ሊነሳ የሚችል ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል፡።
በመሆኑም በነዚህ ዙሪያ ኩባንያዎቻችን ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል ፡፡
በሀገራችን የግሉ ዘርፍ በርካታ ችግሮች ያሉበት እንደሆነ ከተሳታፊዎች ተነሳ ሲሆን ከችግሮቹም መካከል ከፖሊሲ፣ አደረጃጀትና በኩባንያ አቅም ደረጃ የሚገኙት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ተብሏል::
በፖሊሲ ደረጃ ያሉና በአብዛኛው ከንግድ ከባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር የተያያዙትን በተመለከተ በየጊዜው እየታዩ ማስተካከያ የሚደረግባቸውና አሁንም እየተደረገባቸው እንደሚገኙ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ተወካዩ አቶ ታገስ አብራርተዋል፡
በኩባንያ ደረጃ ያሉ ችግሮች ከአደረጃጀት፣ከአሰራርና ከሰው ሀይል ጋር ተያይዘው የሚታዩ መሆናቸውን የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
ይህም የኩባንያዎችን በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ጉዳዮችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠይቃል ብለዋል::
በዚህ ረገድ ኩባንያዎች ጥራት ያለውና ደረጃውን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት በተሳለጠ መንገድ ማቅረብን የሚጠይቅ ይሆናል ብለዋል፡፡
ለዚህም ደጋፊ የሆኑ በርካታ ተቋማትን መፍጠርና ማጠናከር የሚጠይቅ ሲሆን በአጠቃላይ የሀገራችን የግሉ ዘርፍ አቅም ሊጠናከር እንደሚገባና መንግሥስትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ ለነገ የሚባል ባይሆን ይመረጣል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ከተሳታፊዎች ከተነሱት ነጥቦች መካከል በተለይ የነጻ ንግዱ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመተግበር ኢትዮጵያ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ተቋማቷን አሠራር በይበልጥ ማሻሻል ይገባታል ተብሏል፡፡
ከሁለት እጅ በላይ የሚሆነው የኢትጵያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ኢ-መደበኛ በመሆኑ ወደ መደበኛ ማምጣት፣ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መገንባት፣ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን አሁንም መቃኘት፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻል፣ የተረጋጋ ዋጋ እንዲኖር ማድረግ እና ለኢንቨስተሮች በቂ ዋስትና መስጠት እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል ፡፡
ያነጋገርናቸው ተሳታፊዎች እንደጠቆሙት የጥሬ እቃዎች ጥራትና እጥረት፣የማምረቻ ዋጋ ማሻቀብ፣የንግድ ማሳለጫ አገልግሎት ውጤታማ አለመሆን፣የውጪ ምንዛሬ እጥረትና ፣የሀይል መቆራረጥ፣የተጣጣመ የንግድ ፖሊሲ አለመኖር ሌላኛዎቹ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪነት የሚፈታተኑ ናቸውና ቸል ባይባሉ ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ ኩባንያዎች አቅማቸው ሊጠናከር እንደሚገባና መንግሥስትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በዚህ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል አቶ ታገሰ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2026 የአለም የንግድ ድርጅትን እንድትቀላቀል መንግስት እቅድ ይዞ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በቅርቡም አምስተኛውን የድርድር ስብሰባ/ working party meeting/ ታደርጋለች ተብሏል ፡፡