ምክር ቤቱ ዘመኑን የሚመጥን የፖሊሲ ምክረ ሀሳቦችን በማቅረብ የመፍትሔ አካል እንደሚሆን ተነግሯል ።
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት 75ኛ አመት የምስረታ በአሉን በማስመልከት በዛሬው እለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሠጥቷል። የም/ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሠንበት ሸንቁጤ እንደገለፁት የም/ቤቱ 75ኛ የምስረታ በአል ከሰኔ 21-23 2014 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
የም/ቤቱን የ75 አመታት ጉዞ የሚዘክር መጽሐፍ እና የምስል ቅንብር ተዘጋጅቷል የተባለ ሲሆን ውይይቶች እና በም/ቤቱ ላይ አበርክቶ ለነበራቸው ግለሰቦች እውቅና እንደሚሰጥ ተገልጿል ። መላው እንቅስቃሴዎቹ ያተኮሩት ምክር ቤቱ ያለፈባቸውን ውጣ ውረዶች ፣ እድሎችና ተግዳሮቶች ቀጣዩ ትውልድ እንዲያውቃቸው እና እንዲዘክራቸው ማድረግ ሲሆን ተቋሙ በፈተናዎች ውስጥ ህልውናውን አስጠብቆ የቆየበትን ተቋማዊ ምስጢር ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥበት ሁኔታ ይሆናል ፡:
ወ/ሮ መሠንበት የግሉን ዘርፍ እድገት ለማስቀጠል እና የንግድ ስርአቱን ለማዘመን ም/ቤቱ በአዋጅ በተሰጠው ተልእኮ መሠረት በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ መካከል የአገናኝ ድልድይነት ሚናውን የመወጣት ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ዘመኑን የሚመጥን አማራጭ የፖሊሲ ምክረ ሀሳቦችን መስጠትና ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ረገድ የመፍትሔው አካል መሆን ቀጣይነት ያለው የም/ቤቱ የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆን ወ/ሮ መሠንበት ተናግረዋል ።
የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት በ1939 ዓ.ም በቀዳማዊ አፄ ኀይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት በአዋጅ የተቋቋመ ተቋም ነው።
እንደሚታወቀው ጀግኖች አባቶቻችን የፋሺስት ወረራን ቀልብሰው ኢትዮጵያን እንደገና በእግሯ ለማቆም በሚታትሩበት በ1930ዎቹ መጨረሻ ላይ በሀገር ፍቅር ማኅበር ታቅፈው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ነጋዴዎች የንግዱን ዘርፍ አርበኝነት አሃዱ ብለው መጀመራቸው የነበራቸውን አርቆ አስተዋይነት ያሳየናል፡፡
ያኔ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፈቃድ የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ምክር ቤታቸውን ያቋቋሙበት ምክንያትና ዓላማ በንግዱ ማኅበረሰብና በመንግሥት መካከል አገናኝ ድልድይ ሆነው ህጋዊ አግባቦችን ሁሉ በመጠቀም የሀገራችንን የንግድ ሥራን ለማሻሻል የሚበጁ ሀሳቦችን ለማቅረብ እንደነበር ይታወቃል::