የንግዱ ማህበረሰብ በንግድ ምክር ቤት ጥላ ስር በመታቀፍ መብቱንና ጥቅሙን እንዲያስጠብቅ የሚያግዝ የንቅናቄና የግንዛቤ መድረክ ተጀመረ

አዲስ ቻምበር ከቅርብ ወራት ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን በመክፈት፤ የአባላቶቹን ቁጥር የማሳደግ፤ የንግዱን ማህበረሰብ አቅም የማሳድግ እንዲሁም ጠንካራና ተወዳዳሪ የግል ዘርፍ እንዲፈጠር በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

የዚህ አንድ አካል የሆነው የአባላት የክፍለ ከተሞች የንቅናቄና የግንዛቤ ማሳደጊያ መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ በለሚ ኩራ ክ/ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተጀምሯል፡፡

በተካሄደው የግንዛቤ ማሳደጊያ መድረክ ላይ በክፍለ ከተማው የሚገኙ ከ 500 በላይ የሚሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት፤ የክፍለ ከተማው የንግድ ጽ/ቤት እና የገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊዎች፤ የአዲስ ቻምበር ፕሬዚደንትና ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላትና የቅርንጫፍ አስተባባሪዎች ተገኝተዋል፡፡

በዚህ መርኀ ግብር ላይ የአዲስ ቻምበር ፕሬዚደንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ ቁልፍ የሆነ መልክቶችን ያስተላለፉ ሲሆን የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት/ አዲስ ቻምበር/ የግሉን ዘርፍ በማጠናከር በሃገሪቱ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ካለፉት 78 አመታት ጀምሮ የበኩሉን ሚና በመጫወት ላይ የሚገኝ ብቸኛ የከተማችን ንግድ ምክር ቤት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ አክለውም ምክር ቤቱ ጠንካራና በአዋጁ የተሰጠውን ስልጣን እና ኃላፊነት መወጣት የሚያስችለውን ቁመና እንዲላበስ ለማድረግ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከነዚህም መካከል ንግድ ምክር ቤቱ ከተማዋን የሚወክል ማድረግና ተደራሽነቱን ወደ ክፍለ ከተማ እና ወረዳ በመዘርጋት የተደራጀ እና አንድ የግሉ ዘርፍ ድምጽ የሚሆንበት ምክር ቤት ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ካሉት በርካታ የንግድ ማህበረሰብ ውስጥ ወደ 17 ሺህዎቹ ብቻ ለብዙ አመታት በንግድ ምክር ቤቱ በአባልነት ታቅፈው እንደነበር የተናገሩት ወ/ሮ ዘሀራ ይህም ከጠቅላላው የአዲስ አበባ ነጋዴ ቁጥር አንፃር ሲታይ አነስተኛ እና የከተማዋን የንግድ ህብረተሰብ ፍላጎትና ጥቅም ከማስጠበቅና ከመወከል አኳያ ብዙ ጥረትን የሚጠይቅ መሆንን ያስታወሱ ሲሆን ይህን ቁጥር ከፍ በማድረግ ከተማዋን የሚመጥንና የተደራጀ አባል ያለው ንግድ ምክር ቤት እንዲኖር አሁን ያለው አዲሱ የንግድ ምክር ቤት የቦርድ አመራር ውሳኔ በማሳለፍ በሁሉም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ቅርንጫፍ መክፈቱን በመድረኩ ላይ ተናግረዋል፡፡

 

በዚህ መርኀ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ ተ/ዋና ጸሀፊ አቶ ዘካርያስ አሰፋ ስለ ምክር ቤቱ ታሪካዊ አመጣጥ፤ አደረጃጀትና አገልግሎት ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የንግዱ ማህበረሰብ የምክር ቤቱ አባል በመሆን በንግድ አውድ ውስጥ ተወዳዳሪ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

ምክር ቤቱ እየወሰደ ባለው የሪፍርም ስራ ውስጥ የአባላትን ቁጥር ማሳደግ እና ድጋፍ ማድረግ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡

የለሚ ኩራ ንግድ ጸ/ቤት ኃላፊ አቶ ሳሙኤል በበኩላቸው የንግዱ ማህበረሰብ በመደራጀት መብቱን ማስጠበቅ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በንግድ ምክር ቤት ጥላ ስር በመሆን የንግዱ ማህበረሰብ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከመንግስት ጋር በቅርበት በመመካከር ችግሮችን ለመፍታት ቁል ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በዚህ መርኀ ግብር ላይ በመድረኩ የተሳተፉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በንግድ ስራቸው ላይ እያጋጠማቸው ስላለው ዘርፈ ብዙ ችግር ያጋሩ ሲሆን የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትም ሆነ የንግዱ ማህበረሰብ ወኪል የሆነው አዲስ ቻምበር የተነሱ ችግሮችን ምላሽ እንዲያገኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የክፍለ ከተሞች የንቅናቄና የግንዛቤ ማሳደጊያ መድረክ በቀጣይም በሌሎች ክፍለ ከተሞች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመርኀ ግብሩ ላይ ለማወቅ ተችሏል፡፡

wpChatIcon
wpChatIcon