የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከተለያዩ የቴክኒክ እና ሞያ ተቋማት ለተውጣጡ እንዲሁም ስራ ለጀመሩ ወጣቶች በቀጣይ የሚኖራቸውን የስራ ግዜ የተሳካ እንዲሆንላቸው የሚያግዟቸውን ክህሎቶች እንዴት ማዳበር እንዳለባቸው አቅጣጫ የሰጠ ስልጠና አካሄደ ፡፡
የአምራች ዘርፉ የሚፈልገውን ብቁ ባለሞያ አለማግኘትን ተከትሎ የሚከሰተውን ክፍተት ለማጥበብም ሆነ ወጣቶች በሚፈልጉት የስራ መስክ ለመሰማራት እና ውጤታማ ለመሆን ከሰዎችጋር አብሮ የመስራት ፡የመግባባት እንዲሁም ሌሎች ክህሎቶችን ማዳበር እንደሚያፈልጋቸው ተጠቁሟል፡፡
ብዙ ግዜ ወጣቶቹ በሚማሩባቸው ተቋማት የሚጨብጧቸው እውቀቶች በቀጥታ ከሞያቸው ጋር የሚገናኙ መሆናቸውን ተከትሎ ለስራዎቻቸው አስፈላጊ ነገርግን ትኩረት የማይሰጣቸው ክህሎቶች አለመዳበር ውጤታማ እንዳይሆኑ እንቅፋት ስለሚሆኑባቸው፡ተከታታይነት ያለው የክህሎት ስልጠና እንደሚያስፈልጋቸው ስልጠናውን የሰጡት ባለሞያ አቶ ያዛቸው ሞላ ገልጸዋል፡፡
ባለሞያው አክለውም በትምህርት ስርአቱ ውስጥ መሰል አሰራሮች ተካተው የሚፈለገው ደረጃ ላይ እስኪደረስ ድረስ ብቁ ባለሞያ እጥረት እየገጠማቸው ያሉ ኢንዱስትሪዎች ከትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ተማሪዎቹ ጨርሰው ከመውጣታቸው በፊት በስልጠና ሊያግዟቸው እንደሚገባ አንስተው ይህ አሰራር ኢንዱስትሪዎቹ ሰራተኞች በሚቀጥሩበት ግዜ ለማሰልጠን የሚያወጡትን ወጭ እንደሚቀንስላቸው አንስተዋል፡፡
በስልጠናው ለአዳዲስ ስራ ፈጣሪዎች እና ለጀማሪዎች ያለውን አገር አቀፍ አሁናዊ መልካም እድሎች እና ተግዳሮቶች በመዳሰስ ማብራርያ የሰጡት አቶ ኤልያስ ግዛቸው ምንም እንኳን ስራ ፈጣሪዎች ተበረታተው ወደስራ እንዳይገቡ እንቅፋት የሚሆኑ አሰራሮች ቢኖሩም እያደገ የመጣው የህዝብ ቁጥር፡እየተስፋፋ የመጣው የጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ማበልጸግያ ማእከላት እንዲሁም እንደሃገር ስራ ፈጣራ በመንግስት ትኩረት ያገኘ መሆኑ እና የቴክኖሎጂ መስፋፋት፡መልካም እድሎች ሊሆኑት እንደሚችሉ እና ወጣቶቹም ውጤታማ እሆናለው ብለው ባመኑት የስራ ዘርፍ እንዲሰማሩ እድል እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በርካታ ስራዎችን የሚያከናውን ሲሆን ፡ለወጣቶቹ የተሰጠው ስልጠናም ከዳኒሽ ኢንዱስትሪ ኮንፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ነው፡፡