የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ም/ቤት በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 9 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ 500 ለሚሆኑ ዜጎች በኤግዚቢሽን ማዕከል የማዕድ ማጋራት አካሂዷል፡፡
አዲስ ቻምበር ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት የክረምት ፕሮጀክት ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
የግሉ ዘርፍ ጥምረት በኑሮ ውድነት ላይ በሚል ከሚያካሂዳቸው መካከል አንዱ የምገባ መርሃግብር ነው፡፡
የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበር ሸንቁጤ በዚህ ወቅት እንዳሉት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ዜጎች ምግብ ማጋራት የም/ቤቱ የአጭር ጊዜ እቅድ አካል ነው፡፡
በቀጣይም ም/ቤቱ ይህን በጎ አላማ እንደሚያከናውን ጠቁመው በመካከለኛ እና በረዥም ጊዜ እቅዱ ደግሞ አቅም የሌላቸው ስራ አጥ ወጣቶችን በተደራጀ መልኩ የስራ እድል ፈጠራ የማመቻቸት ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
የአዲስ ቻምበር ዋና ፀሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በበኩላቸው ከምሳ ምገባ በተጨማሪ ደረቅ ምግቦች እንደ ፓስታ፣ መኮሮኒ፣እና ዘይት የመሳሰሉ ምግቦች ከከተማው አስተዳደር ጋር በመቀናጀት ለአቅመ ደካሞች እንዲደርሳቸው ይደረጋል ብለዋል፡፡
ም/ቤቱ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በዝቅተኛ ደሞዝ ለሚተዳደሩ የኩባንያ ሰራተኞች በደሞዛቸው ላይ ድጎማ እንዲያገኙ እንሰራለን ብለዋል፡፡
የቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚና የስራ ኢንተርፕራይዝ ኢንዱስትሪ ልማት ፅ/ቤት ሃላፊ ወ/ሮ ወርቅነሽ ቢረዳ ለአዲስ ቻምበር በጎ አድራጎት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በተለይም በወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ዙርያ ከአዲስ ቻምበር ጋር በጋራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡