ያለግሉ ዘርፍ ጠንካራ ተሳትፎ አረንጓዴ ሽግግርን ማሳካት እንደማይቻል ተጠቁሟል::
ምክር ቤቱ ከዳኒሽ ኮንፌዴሬሽን ኢንደስትሪ በተገኘ ድጋፍ አረንጓዴ ሽግግር ላይ ትኩረት በማድረግ ያስጠናውን ጥናት በባለሞያዎች አስተችቷል፡፡
የአረንጓዴ ሽግግር ፍኖተ ካርታ የአየር ንብረት ለውጥ አለም አቀፍ አጀንዳ መሆኑን ተከትሎ ተጽኖው ኢትዮጵያን በመሰሉ ታዳጊ ሃገራት ላይም ከፍተኛ በመሆኑ ለማንቃት እና አቅጣጫ ለማሳየት ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የንግድ ስራ በተለመደው መልኩ ከቀጠለ ዘላቂነቱን ጥያቄ ውስጥ ስለሚከተው የአረንጓዴ ሽግግርን ታሳቢ ያደረገ የንግድ ስራ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡
የኢኮኖሚ እድገት ከባቢ ሁኔታን በማጥፋት እና ማህበረሰብን ዋጋ በማስከፈል መምጣት የሌለበት በመሆኑ ፡የኢኮኖሚ እድገት ፡ከባቢ ሁኔታ እና ማህበረሰብ ተደጋግፎ እና ተጣጥሞ መሄድ መቻልም አለበትም ተብሏል፡፡
ፍኖተ ካርታው 80 በመቶ የሚሆኑ የአዲስ አበባ እና በአካባቢዋ የሚገኙ ማህበረሰቦች እና የንግድ ስራዎች አረንጓዴ ሽግግርን ታሳቢ ያደረጉ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ማስቻልን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን መንግስት እና የግሉ ዘርፍ በጋራ በመሆን አረንጓዴ ሽግግርን ታሳቢ ያደረጉ ፖሊሲዎች መዘጋጀት እንዲችሉ የሚያግዝ እና ከማህበረሰብ ጋር አብሮ ለመስራት የሚቻልበትንም መንገድ የሚያሳይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የዜጎችን ኑሮ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገር ፡የስራ አድል ለመፍጠር የግሉ ዘርፍ ሰፊ ድርሻ ያለው ከመሆኑ አንጻር በአረንጓዴ ሽግግር ዙርያ የተሻለግንዛቤ ኖሮት በእቅዶቻቸው ውስጥ ማካተት እንደሚያስፈልጋቸውም ተነስቷል፡፡
ለዘላቂ ልማት የአየር ንብረት ለውጥ አንዱ ጉዳይ ሲሆን ሌሎች ተያያዥ ትኩረት የሚፈልጉ ማህበራዊ ሃላፊነትን መወጣት፡መልካም አስተዳደር እና ሌሎችንም የሚያቅፍ በመሆኑ ቀጣይነት ላለው ንግድ ስራ ሃላፊነት በተመላበት መልኩ በማከናወን ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ንግድ ምክር ቤቱ ሃላፊነት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡
ምክር ቤቱ ያዘጋጀው ፍኖተ ካርታም መነሻው በአዲስ አበባ ከተማ ይሁን እንጂ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚሰፋ መሆኑም ተብራርቷል፡፡