የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል የንግዱ ማህበረሰብ አቅሙ እንዲገነባና ተወዳዳሪ እንዲሆን በማስቻል ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ማገዝ ነው፡፡
ከዚህ አኳያ ንግድ ምክር ቤቱ ከኤስ ኤ ኬ የስልጠና እና የማማከር ተቋም ጋር በጋራ በመተባበር የስራ መሪዎች መድረክ / Forum for ExEcutive Leaders/ FEEL የተሰኘ አዲስ የመማማሪያ፣ የልምድ ልውውጥ እና የግንኙነት መረብ (Networking) ማዳበር ላይ መሰረት ያደረገ አገልግሎት ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት አጠናቋል ፡፡
ይህ የቢዝነስ መሪዎች ምርጥ ልምድና ተሞክሮ የሚዳሰስበትና አዳዲስም ሆነ በስራ ላይ ያሉ የቢዝነስ የስራ መሪዎችን እና ስራ ፈጣሪዎችን የሚያነቃቃ የተሞክሮ ልውውጥ መድረክ በቀጣዩ የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም በርካታ የስራ መሪዎች እና ባለድርሻ አካላት በሚገኙበት በይፋ ይጀመራል ፡፡
ይህ አገልግሎት የቢዝነስ ባለቤቶችን በኩባንያ መልካም አስተዳደር እንዲቃኙ ያበረታታል፤ንግድ እና ቢዝነስን ሊጎዱ የሚችሉ ሁኔታዎችን ፖሊሲ አውጪዎችን እና ባለሀብቶችን ያልታዩ አጋጣሚዎችን በማሳየት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያመላክታል፡፡
መድረኩም በዋነኛነት፣
• በተለያየ መስክ ለተሰማሩ የሥራ መሪዎች ምቹ የመማማሪያ ሁኔታ ለመፍጠር፣
• መልካም ተሞክሮ ካላቸው መሪዎች ተግባር ተኮር እና አዳዲስ ሐሳቦችን እንዲያገኙ ለማስቻል፣
• በመሪዎች መካከል የግንኙነት መረብ እንዲዳብር እና የመሪነት ሙያ እንዲጎለብት ማስቻል
• ወደፊት የመሪነት ቦታ ለመያዝ የሚታጩ ወጣት መሪዎች ከአንጋፋ መሪዎች የመሪነትን ጥበብ አንዲላበሱ ማገዝ
• በአመራር ላይ ስኬታማ በመሆን ታዋቂ የሆኑ ታላላቅ ዜጎች (senior citizens) ለስራቸው እውቅና የሚሰጥበት መድረክ አንዲሆን ማድረግ
በአንድ ጊዜ ከሰማንያ በላይ የቢዝነስ ስራ መሪዎች የሚታደሙበት ይህ የልምድ ልውውጥ መድረክ ህብረተሰቡ የራሴ የሚለውን ቢዝነስ ተነቃቅቶ እንዲጀምርና አዳዲስ የስራ ዕድል እንዲከፍት መንገድ ያመላክታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን የቢዝነስ ሰዎችን በተለያዩ መድረኮች በመጋበዝ ቢዝነሱን እንዴት እንደ ጀመሩ፤እንደመሩት እንዲሁም ተግዳሮትን አልፈው አዋጪና አትራፊ እንዳረጉ በታዳሚያን ፊት ቀርበው ያስረዳሉ፡፡
በዚህ መድረክ የታላላቅ የስራ አስፈጻሚዎች የቢዝነስ አስተሳሰብ እንዲቃኝ በማድረግ ምርጥ ተሞክሮዎቻቸውና ስኬቶቻቸው ለአሁኑ ትውልድ እንዲተላለፉ ይደርጋል ፡፡
ታላላቅ የሀገራችን የስራ መሪዎች ባለፉባቸው የአመራር ዘመናት ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ሲገጥማቸው የነበሩ የኢኮኖሚና የቢዝነስ ተግዳሮቶች እንዴት እንደተወጡ ለሥራ መሪዎች አቅጣጫም ይጠቁማሉ፡፡
በመሆኑም የንግዱ ህብረተሰብ በእውቀት ላይ የተደገፈ የንግድ ስራ ውሳኔ እንዲያደርጉ በማስቻል፣ ወጣትና አዳዲስ የንግድ ስራ መሪዎች የላቀ ተሞክሮ ካላቸው መሪዎች የአመራር ጥበብ እና ዘዴዎችን በመቅሰም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡
የመጀመሪያውን ዙር ልምድ የሚያካፍሉት የቀድሞው የሚድሮ ቶክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ እና በአሁኑ ወቅት የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር አረጋ ይርዳው ሲሆኑ ቀኑም የካቲት 21 ፤ 2016 ይሆናል፡፡
መድረኩ በወር አንድ ጊዜ የሚካሄድ ሆኖ ለሁለት ሰዓት የሚቀይ ሲሆን ከሰዓት በኋላ ከ11፡30 እስከ ምሽቱ 1፡30 በቋሚነት የሚሰጥ ይሆናል፡፡
የንግድ ተቋማት መድረኩ አቅም ግንባትን ለማዳበር ያለውን ፋይዳ በማወቅ በአሁኑ ወቅት ስራ አመራር ሃላፊነት ላያ ያሉ መሪዎችን ወይም ወደፊት መሪ ለመሆን የታጩትን ወጣቶች ወደ መድረኩ በመላክ ብቃታቸውን አንዲገነቡ እድል እንዲያመቻቹላቸው አዘጋጆች መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡
በተጨማሪም ማንኛውም የአላማው ደጋፊ፤ የስራ መሪ፤ የንግድ አከናዋኞች እና የስራ ፈጣሪዎች የዚህ መድረክ አካል እና ተሳታፊ መሆን እንደሚችሉ አዘጋጆቹ በአክብሮት ይጋብዛሉ፡፡
በመጨረሻም የቢዝነስም ሆነ ሌሎች ተቋማት ይህንን ከፍተኛ አመራሮች የሚገኙበት የእውቀት ሽግርግር እና የግንኙነት መረብ የሚዳብርበት (የኔትወርኪንግ) መድረክ ሰፖንሰር በማድረግ ምርት እና አገልግሎታቸውን በማስተዋወቅ በማህበረሰቡ መልካም ዝናቸውን መገንባት አንዲችሉ አዘጋጆች መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡
አዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና
ኤስ ኤ ኬ የስልጠና እና የማማከር ተቋም