በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ድልድይ ፊት ለፊት የሚገኙ ሱቆች ለመንገድ ማስፋፊያ በሚል ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ይፍረሱ መባሉ እንዳሳዘናቸው ነጋዴዎች ገለፁ ፡፡
በከፍያለው ዋሲሁን
በቦሌ አየር መንገድ ፊት ለፊት የሚገኙት ባለ አንድ ፎቅ የንግድ ቤቶች ፣ፋርማሲዎች ፣ ካፌዎች እና በንግድ አግልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎች የስራ ቦታቸው በአስቸኳይ እንዲፈርስ እየተደረገ መሆኑ ትክክል እንዳልሆነ በአካባቢው ሱቆችን ተከራይተው የሚሰሩ እና የንግድ ቤት ባለቤቶች ለአዲስ ቻምበር ሚዲያ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ ቻምበር ሚዲያም በአካል በቦታው በመገኝት ለመመልከት ችሏል ፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ቦታው ለልማት መፈለጉ እንዳለ ሆኖ በአስቸኳይ ይፍረሱ መባሉ እና በአጭር ቀነገደብ ውስጥ መሆን አልነበረበትም ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ግለሰቦች ለዘመናት ለፍተው ያፈሯቸው ንብረቶቻውን በምን ሁኔታ እንደሚለቁ እና እንደሚያፈርሱ ግልጽ ሳይደረግ ድርጊቱ በችኮላ መፈጸሙ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትና ካሳ የሚከፈልበት ሁኔታን ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ሊጻረር የሚችል አካሄድ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ አበራ አበጋዝ ለአዲስ ቻምበር ሚዲያ እንደገለጹት ልማት መኖር የለበትም እያልን ሳይሆን የንግድ ሱቆች በመፍረሳቸው ለተጎዱ ባለንብረቶች የሚገኙ ጥቅሞችና ጉዳቶች በአዋጁ መሰረት ሊታወቅ የሚገባ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ሳይነገረን ወደ ፈረሳ መግባቱ አግባብነት የለውም ብለዋል ፡፡
የንግድ ማህበረሰብ ድምፅ የሆነው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የተቋቋመው የንግድ ህብረተሰብን ጥቅምና ፍላጎት ለማስከበር መሆኑን ያነጋገርናቸው የንግድ ድርጅቶች ጠቁመው ይህንን ጉዳይ ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡ ፡
በመሆኑም ንግድ ምክር ቤቱ ያለውን ከፍተኛ ተሰሚነት ለወረዳውም ፣ ለክፍለ ከተማው እንዲሁም ከንቲባ ጽ/ቤት በማሳወቅ ድምፃቸውን እንዲያሰማለቸው ጠይቀዋል ፡፡
አዲስ ቻምበር በንግዱ ማህበረሰብ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት የጋራ መፍትሄና ምክክር ለማድረግ ይቻል ዘንድ በቀጣይ ጉዳዩን አስመልክቶ የምክክር መድረክ ለማዘጋጀት በዝግጅት ላይ ይገኛል ፡ ፡