አዲስ ቻምበር ከኢትዮጵያ ቡና ማሕበር ጋር የመግባቢያ ሠነድ ተፈራረመ

አዲስ ቻምበር ከኢትዮጵያ ቡና ማሕበር ጋር የመግባቢያ ሠነድ ተፈራረመ
በይድነቃቸው ዓለማየሁ
በሁለቱ ወገኖች በኩል በተፈረመው ሠነድ መሠረት ንግድ ምክር ቤቱ በአድቮከሲ፤በጥናት እና ምርምር እንዲሁም በስልጠና መስክ ለማሕበሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
በስነ-ሥርዓቱ ላይ የአዲስ ቻምበር ፕሬዝደንት ወ/ሮ መሠንበት ሸንቁጤ አዲስ ቻምበር የዓለም ንግድ ም/ቤት አባል እንደመሆኑ መጠን ከተለያዩ ባለድርሻዎች ጋር በመነጋገር በአሁኑ ሰዓት በቡና የወጪ ንግድ ላይ የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ የበኩሉን ጥረት ያደርጋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ማሕበር ፕሬዝደንት አቶ ደሳለኝ አጀመ በበኩላቸው ማሕበራቸው ከአንጋፋው ንግድ ም/ቤት ጋር በጋራ መሥራት በመቻሉ ደስታ ይሰማዋል ብለዋል፡፡
ንግድ ም/ቤቱ እና ማሕበሩ የግሉ ዘርፍ አካል በመሆናቸው እና በአገራችን ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ሚና ያላቸው እንዲሁም ተዛማጅ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ናቸው ተብሏል፡፡
ስለዚህ የስምምነቱ ሠነድ ሁለቱም ወገኖች እየተናበቡ ተመጋጋቢ ሥራዎችን ለማከናወን ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ማሕበሩ በቡና ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ ባለድርሻዎች በተሳተፉበት የውይይት መድረክ ላይ በየመን የሚንቀሳቀሱት የሃውቲ ታጣቂዎች በመርከቦች ላይ በሚሰነዝሩት ጥቃት ሳቢያ በቀይ ባሕር ንግድ መስመር ላይ ውጥረት መንገሱ ተወስቷል፡፡
በተፈጠረው የንግድ ስጋት ሳቢያ ዋና ዋና የጭነት መርከብ ኩባንያዎች ወደ ጂቡቲ ወደብ የሚያደርጉትን ጉዞ ማቆማቸው ተነግሯል፡፡
ለችግሩ መላ ለማፈላለግ አንድ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን እና ኮሚቴውም በቅርቡ ለመንግስት የውሳኔ ሃሳብ እንደሚያቀርብ የማሕበሩ ባለሥልጣናት ገልጸዋል፡፡